ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤፌሶን 6:8-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ምክንያቱም፣ ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ።

9. እናንተም ጌቶች ሆይ፤ ለባሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የእነርሱም፣ የእናንተም ጌታ የሆነው በሰማይ እንዳለ፣ የሰውንም ፊት አይቶ እንደማያደላ ታውቃላችሁና አታስፈራሯቸው።

10. በተረፈ በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ።

11. የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ።

12. ምክንያቱም ተጋድሎአችን ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋር ነው።

13. ክፉው ቀን ሲመጣ መቋቋም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ፤ ሁሉን ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁና።

14. እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፣

15. በሰላም ወንጌል ዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ።

16. ከእነዚህም ሁሉ ጋር፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤

17. የመዳንን ራስ ቊር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።

18. በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ።

19. የወንጌልን ምስጢር ለመግለጥ አፌን በምከፍትበት ጊዜ ሁሉ በድፍረት እንድናገር ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ጸልዩልኝ።

20. በሰንሰለት የታሰረ መልእክተኛ የሆንሁት ለዚሁ ነውና። ስለዚህ መናገር የሚገባኝን ያለ ፍርሀት እንድናገር ጸልዩልኝ።

21. በምን ሁኔታ እንዳለሁና ምን እንደማደርግ ታውቁ ዘንድ ተወዳጅ ወንድምና በጌታ ታማኝ አገልጋይ የሆነው ቲኪቆስ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል።

22. የእኛን ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያበረታ ለዚሁ ስል ወደ እናንተ ልኬዋለሁ።

23. ከእግዚአብሔር አብ፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም፣ ፍቅርም ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤፌሶን 6