ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 18:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ብርድ ስለ ነበር አገልጋዮቹና ሎሌዎቹ ባያያዙት የከሰል ፍም ዙሪያ ለመሞቅ ቆመው ሳሉ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር።

19. በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው።

20. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ፤ አይሁድ በተሰበሰቡበት ምኵራብ፣ በቤተ መቅደስም ሁል ጊዜ አስተምሬአለሁ፤ በስውር የተናገርሁት የለም።

21. ለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እነሆ፤ የተናገርሁትን እነርሱ ያውቃሉ።”

22. ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ፣ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ፣ “ለሊቀ ካህናቱ የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ በጥፊ መታው።

23. ኢየሱስም፣ “ክፉ ተናግሬ ከሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ እውነት ከተናገርሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው።

24. ሐናም ኢየሱስ ታስሮ እንዳለ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው።

25. ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ሲሞቅ፣ “አንተ ከእርሱ ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አሉት።እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል ካደ።

26. ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ፣ “በአትክልቱ ስፍራ አንተን ከእርሱ ጋር አላየሁህም?” ሲል ጠየቀው።

27. ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።

28. አይሁድም ኢየሱስን ከቀያፋ ወደ ሮማዊው ገዥ ግቢ ይዘውት ሄዱ፤ ጊዜውም ማለዳ ነበር። አይሁድም ፋሲካን መብላት እንዲችሉ፣ ላለመርከስ ወደ ገዥው ግቢ አልገቡም።

29. ስለዚህ ጲላጦስ ወደ እነርሱ ወጥቶ፣ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው።

30. እነርሱም፣ “ይህ ሰው ወንጀለኛ ባይሆን ኖሮ፣ አንተ ፊት ባላቀረብነውም ነበር” ብለው መለሱለት።

31. ጲላጦስም፣ “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው።አይሁድም፣ “እኛማ በማንም ላይ የሞት ፍርድ ለመፍረድ መብት የለንም” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 18