ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 14:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. በመሬት ላይ የፈሰሰ ውሃ እንደማይታፈስ ሁሉ፣ እኛም እንደዚሁ እንሞታለን፤ እግዚአብሔር ግን ከአገር የተሰደደ ሰው ከእርሱ እንደ ራቀ በዚያው እንዳይቀር የሚመለስበትን ሁኔታ ያመቻቻል እንጂ ሕይወቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም።

15. “አሁንም ወደዚህ የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ይህንኑ ለንጉሥ ጌታዬ ለመንገር ነው። እኔም አገልጋይህ ይህን አሰብሁ፤ ‘ለንጉሡ እነግረዋለሁ፤ ምናልባትም አገልጋዩ የጠየቀችውን ይፈጽምላት ይሆናል፤

16. እግዚአብሔር ከሰጠን ርስት እኔንም ልጄንም ሊነቅለን ከተነሣው ሰው እጅ ንጉሡ አገልጋዩን ሊታደግ ይፈቅድ ይሆናል።’

17. “አሁንም አገልጋይህ፤ ‘ንጉሥ ጌታዬ በጎውንና ክፉውን በመለየት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆነ፣ የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኝ፤ እግዚአብሔር አምላክህም ካንተው ጋር ይሁን’ ትላለች።”

18. ከዚያም ንጉሡ ሴቲቱን፣ “እኔም ለምጠይቅሽ ነገር አንቺም መልሱን አትደብቂኝ” አላት።ሴቲቱም፣ “ንጉሥ ጌታዬ፤ እሺ ይናገር” አለችው።

19. ንጉሡም፣ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ የለበትምን?” ሲል ጠየቃት።ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከተናገረው ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም የሚል ማንም የለም። አዎን ይህን እንዳደርግ ያዘዘኝና ይህም ሁሉ ቃል በእኔ በአገልጋይህ አንደበት እንዲነገር የላከኝ አገልጋይህ ኢዮአብ ነው።

20. አገልጋይህ ኢዮአብ ይህን ያደረገውም ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ሲል ነው፤ ነገር ግን ጌታዬ የእግዚአብሔርን መልአክ ጥበብ የመሰለ ጥበብ ስላለው፣ በምድሪቱ ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ያውቃል።”

21. ንጉሡም ኢዮአብን፣ “መልካም ነው፤ ፈቅጃለሁ፤ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 14