ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አቤሴሎም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ

1. የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ ተረዳ።

2. ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ቴቁሔ፤ ሰው ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፤ “ሐዘንተኛ በመምሰል የሐዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይት አትቀቢ፤ ለሞተ ሰው ብዙ ጊዜ እንዳዘነች ሴት መስለሽም ታዪ።

3. ከዚያም ወደ ንጉሡ ሄደሽ እንዲህ በዪው።” ከዚያም ኢዮአብ የምትናገራቸውን ቃላት ነገራት።

4. የቴቁሔዪቱም ሴት ወደ ንጉሡ ገብታ፣ በንጉሡ ፊት ወደ መሬት በግምባሯ ተደፍታ እጅ በመንሣት አክብሮቷን ከገለጠች በኋላ፣ “ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ” አለች።

5. ንጉሡም፣ “ችግርሽ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃት።እርሷም እንዲህ አለች፤ “እኔ በእርግጥ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ፤

6. እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ ገላጋይም ስላልነበረ፣ አንዱ ሌላውን መትቶ ገደለው።

7. እነሆ ቤተ ዘመዱ ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው፣ ‘ወንድሙን ስለ ገደለ እንገድለዋለንና ወንድሙን የገደለውን ሰው አሳልፈሽ ስጪን፣ ከዚያም ወራሽ አልባ ትሆኛለሽ’ ይሉኛል፤ ስለዚህ የቀረኝን አንዱን መብራቴን አጥፍተው፣ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው።”

8. ንጉሡም ሴቲቱን፣ “አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ ስለ ጒዳይሽ አስፈላጊውን ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት።

9. ነገር ግን የቴቁሔዪቱም ሴት፣ “ንጉሥ ጌታዬ፣ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተ ሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች።

10. ንጉሡም፣ “ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢናገርሽ እኔ ዘንድ አምጪው፤ ዳግም አያስቸግርሽም” ሲል መለሰላት።

11. እርሷም፣ “ደም ተበቃዮቹ ልጄን በማጥፋት የባሰ ጒዳት እንዳያደርሱ፣ ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን ይለምን” አለች።ንጉሡም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ከልጅሽ ራስ ላይ አንዲት ጠጒር እንኳ አትነካም” አላት።

12. ከዚያም ሴቲቱ፣ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም፣ “እሺ ተናገሪ” አላት።

13. ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለችው፣ “እንዲህ ያለውን ነገር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያሰብኸው ለምንድን ነው? ንጉሡ ከአገር የተሰደደውን ልጁን አልመለሰውም፤ ታዲያ ይህን ሲናገር በራሱ ላይ መፍረዱ አይደለምን?

14. በመሬት ላይ የፈሰሰ ውሃ እንደማይታፈስ ሁሉ፣ እኛም እንደዚሁ እንሞታለን፤ እግዚአብሔር ግን ከአገር የተሰደደ ሰው ከእርሱ እንደ ራቀ በዚያው እንዳይቀር የሚመለስበትን ሁኔታ ያመቻቻል እንጂ ሕይወቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም።

15. “አሁንም ወደዚህ የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ይህንኑ ለንጉሥ ጌታዬ ለመንገር ነው። እኔም አገልጋይህ ይህን አሰብሁ፤ ‘ለንጉሡ እነግረዋለሁ፤ ምናልባትም አገልጋዩ የጠየቀችውን ይፈጽምላት ይሆናል፤

16. እግዚአብሔር ከሰጠን ርስት እኔንም ልጄንም ሊነቅለን ከተነሣው ሰው እጅ ንጉሡ አገልጋዩን ሊታደግ ይፈቅድ ይሆናል።’

17. “አሁንም አገልጋይህ፤ ‘ንጉሥ ጌታዬ በጎውንና ክፉውን በመለየት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆነ፣ የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኝ፤ እግዚአብሔር አምላክህም ካንተው ጋር ይሁን’ ትላለች።”

18. ከዚያም ንጉሡ ሴቲቱን፣ “እኔም ለምጠይቅሽ ነገር አንቺም መልሱን አትደብቂኝ” አላት።ሴቲቱም፣ “ንጉሥ ጌታዬ፤ እሺ ይናገር” አለችው።

19. ንጉሡም፣ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ የለበትምን?” ሲል ጠየቃት።ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከተናገረው ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም የሚል ማንም የለም። አዎን ይህን እንዳደርግ ያዘዘኝና ይህም ሁሉ ቃል በእኔ በአገልጋይህ አንደበት እንዲነገር የላከኝ አገልጋይህ ኢዮአብ ነው።

20. አገልጋይህ ኢዮአብ ይህን ያደረገውም ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ሲል ነው፤ ነገር ግን ጌታዬ የእግዚአብሔርን መልአክ ጥበብ የመሰለ ጥበብ ስላለው፣ በምድሪቱ ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ያውቃል።”

21. ንጉሡም ኢዮአብን፣ “መልካም ነው፤ ፈቅጃለሁ፤ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው።

22. ኢዮአብም አክብሮቱን ለንጉሡ ለመግለጥ ወደ መሬት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡንም ባረከ፣ ኢዮአብም በመቀጠል፣ “ንጉሡ የአገልጋዩን ልመና ስለ ተቀበለው፣ ባሪያህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቱን ዛሬ ለማወቅ ችሎአል” አለ።

23. ከዚያም ኢዮአብ ወደ ጌሹር ሄዶ አቤሴሎምን ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ አመጣው።

24. ንጉሡ ግን፣ “እዚያው እቤቱ ይሂድ፤ ዐይኔን ማየት የለበትም” አለ። ስለዚህም አቤሴሎም ወደ ቤቱ ሄደ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም።

25. መቼም በመልኩ ማማር አቤሴሎምን የሚያህል አንድም ሰው በመላው እስራኤል አልነበረም፤ ከራስ ጠጒሩ እስከ እግር ጥፍሩ የሚወጣለት እንከን አልነበረም።

26. የራስ ጠጒሩ ሲከብደው በዓመት አንድ ጊዜ ይቈርጠው ነበር፤ የተቈረጠውን በሚመዝነው ጊዜ ክብደቱ በቤተ መንግሥቱ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ይሆን ነበር።

27. አቤሴሎም ሦስት ወንዶች ልጆችና ትዕማር የተባለች አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፤ ሴት ልጁም በጣም ውብ ነበረች።

28. አቤሴሎም የንጉሡን ዐይን ሳያይ ሁለት ዓመት በኢየሩሳሌም ኖረ።

29. ከዚያም አቤሴሎም ወደ ንጉሡ እንዲሄድለት ኢዮአብን አስጠራው፤ ኢዮአብ ግን ወደ እርሱ መምጣት አልፈለገም፤ ለሁለተኛ ጊዜም ላከበት፤ ኢዮአብ አሁንም መምጣት አልፈለገም።

30. ከዚያም አቤሴሎም ለአገልጋዮቹ “ተመልከቱ የኢዮአብ ዕርሻ የሚገኘው ከእኔ ዕርሻ አጠገብ ነው፤ በዕርሻው ላይ የገብስ አዝመራ አለው፤ ሄዳችሁም እሳት ልቀቁበት” አላቸው። ስለዚህ የአቤሴሎም አገልጋዮች ሄደው የኢዮአብን ዕርሻ በእሳት አቃጠሉት።

31. ከዚያም ኢዮአብ ወደ አቤሴሎም ቤት ሄደ፣ “አገልጋዮችህ ለምንድን ነው ዕርሻዬን ያቃጠሉት?” ብሎ ጠየቀው።

32. አቤሴሎምም፣ ኢዮአብን፣ “ከጌሹር ለምን መጣሁ? ለእኔ እስካሁንም እዚያው ብሆን ይሻለኝ ነበር ብሎአል ብለህ እንድትነግርልኝ ‘ወደ ንጉሡ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ና’ ብዬ አስጠራሁህ፤ አሁንም ቢሆን፤ የንጉሡን ዐይን ማየት እፈልጋለሁ፤ ምንም ዐይነት በደል ከተገኘብኝ ይግደለኝ” አለው።

33. ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ሄዶ ይህንኑ ነገረው። ከዚያም ንጉሡ አቤሴሎምን አስጠራው፤ እርሱም መጥቶ በንጉሡ ፊት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።