ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 14:16-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. እግዚአብሔር ከሰጠን ርስት እኔንም ልጄንም ሊነቅለን ከተነሣው ሰው እጅ ንጉሡ አገልጋዩን ሊታደግ ይፈቅድ ይሆናል።’

17. “አሁንም አገልጋይህ፤ ‘ንጉሥ ጌታዬ በጎውንና ክፉውን በመለየት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆነ፣ የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኝ፤ እግዚአብሔር አምላክህም ካንተው ጋር ይሁን’ ትላለች።”

18. ከዚያም ንጉሡ ሴቲቱን፣ “እኔም ለምጠይቅሽ ነገር አንቺም መልሱን አትደብቂኝ” አላት።ሴቲቱም፣ “ንጉሥ ጌታዬ፤ እሺ ይናገር” አለችው።

19. ንጉሡም፣ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ የለበትምን?” ሲል ጠየቃት።ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከተናገረው ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም የሚል ማንም የለም። አዎን ይህን እንዳደርግ ያዘዘኝና ይህም ሁሉ ቃል በእኔ በአገልጋይህ አንደበት እንዲነገር የላከኝ አገልጋይህ ኢዮአብ ነው።

20. አገልጋይህ ኢዮአብ ይህን ያደረገውም ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ሲል ነው፤ ነገር ግን ጌታዬ የእግዚአብሔርን መልአክ ጥበብ የመሰለ ጥበብ ስላለው፣ በምድሪቱ ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ያውቃል።”

21. ንጉሡም ኢዮአብን፣ “መልካም ነው፤ ፈቅጃለሁ፤ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው።

22. ኢዮአብም አክብሮቱን ለንጉሡ ለመግለጥ ወደ መሬት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡንም ባረከ፣ ኢዮአብም በመቀጠል፣ “ንጉሡ የአገልጋዩን ልመና ስለ ተቀበለው፣ ባሪያህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቱን ዛሬ ለማወቅ ችሎአል” አለ።

23. ከዚያም ኢዮአብ ወደ ጌሹር ሄዶ አቤሴሎምን ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ አመጣው።

24. ንጉሡ ግን፣ “እዚያው እቤቱ ይሂድ፤ ዐይኔን ማየት የለበትም” አለ። ስለዚህም አቤሴሎም ወደ ቤቱ ሄደ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም።

25. መቼም በመልኩ ማማር አቤሴሎምን የሚያህል አንድም ሰው በመላው እስራኤል አልነበረም፤ ከራስ ጠጒሩ እስከ እግር ጥፍሩ የሚወጣለት እንከን አልነበረም።

26. የራስ ጠጒሩ ሲከብደው በዓመት አንድ ጊዜ ይቈርጠው ነበር፤ የተቈረጠውን በሚመዝነው ጊዜ ክብደቱ በቤተ መንግሥቱ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ይሆን ነበር።

27. አቤሴሎም ሦስት ወንዶች ልጆችና ትዕማር የተባለች አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፤ ሴት ልጁም በጣም ውብ ነበረች።

28. አቤሴሎም የንጉሡን ዐይን ሳያይ ሁለት ዓመት በኢየሩሳሌም ኖረ።

29. ከዚያም አቤሴሎም ወደ ንጉሡ እንዲሄድለት ኢዮአብን አስጠራው፤ ኢዮአብ ግን ወደ እርሱ መምጣት አልፈለገም፤ ለሁለተኛ ጊዜም ላከበት፤ ኢዮአብ አሁንም መምጣት አልፈለገም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 14