ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 14:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ ገላጋይም ስላልነበረ፣ አንዱ ሌላውን መትቶ ገደለው።

7. እነሆ ቤተ ዘመዱ ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው፣ ‘ወንድሙን ስለ ገደለ እንገድለዋለንና ወንድሙን የገደለውን ሰው አሳልፈሽ ስጪን፣ ከዚያም ወራሽ አልባ ትሆኛለሽ’ ይሉኛል፤ ስለዚህ የቀረኝን አንዱን መብራቴን አጥፍተው፣ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው።”

8. ንጉሡም ሴቲቱን፣ “አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ ስለ ጒዳይሽ አስፈላጊውን ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት።

9. ነገር ግን የቴቁሔዪቱም ሴት፣ “ንጉሥ ጌታዬ፣ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተ ሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች።

10. ንጉሡም፣ “ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢናገርሽ እኔ ዘንድ አምጪው፤ ዳግም አያስቸግርሽም” ሲል መለሰላት።

11. እርሷም፣ “ደም ተበቃዮቹ ልጄን በማጥፋት የባሰ ጒዳት እንዳያደርሱ፣ ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን ይለምን” አለች።ንጉሡም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ከልጅሽ ራስ ላይ አንዲት ጠጒር እንኳ አትነካም” አላት።

12. ከዚያም ሴቲቱ፣ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም፣ “እሺ ተናገሪ” አላት።

13. ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለችው፣ “እንዲህ ያለውን ነገር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያሰብኸው ለምንድን ነው? ንጉሡ ከአገር የተሰደደውን ልጁን አልመለሰውም፤ ታዲያ ይህን ሲናገር በራሱ ላይ መፍረዱ አይደለምን?

14. በመሬት ላይ የፈሰሰ ውሃ እንደማይታፈስ ሁሉ፣ እኛም እንደዚሁ እንሞታለን፤ እግዚአብሔር ግን ከአገር የተሰደደ ሰው ከእርሱ እንደ ራቀ በዚያው እንዳይቀር የሚመለስበትን ሁኔታ ያመቻቻል እንጂ ሕይወቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም።

15. “አሁንም ወደዚህ የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ይህንኑ ለንጉሥ ጌታዬ ለመንገር ነው። እኔም አገልጋይህ ይህን አሰብሁ፤ ‘ለንጉሡ እነግረዋለሁ፤ ምናልባትም አገልጋዩ የጠየቀችውን ይፈጽምላት ይሆናል፤

16. እግዚአብሔር ከሰጠን ርስት እኔንም ልጄንም ሊነቅለን ከተነሣው ሰው እጅ ንጉሡ አገልጋዩን ሊታደግ ይፈቅድ ይሆናል።’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 14