ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 7:20-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. “ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህን አንተ ታውቀዋለህና!

21. ስለ ቃልህና እንደ ልብህ ሐሳብ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ ባሪያህም እንዲያውቀው ገልጸህለታል።

22. ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት ታላቅ ነህ! ከቶ የሚመስልህ ማንም የለም፤ በጆሮአችን እንደ ሰማነው ሁሉ፣ ከአንተ በቀር አምላክ የለም።

23. ለራሱ ሕዝብ ይሆን ዘንድ ሊታደገው፣ እግዚአብሔር በፊቱ እንደሄደለት ሕዝብ፣ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና አማልክቶቻቸውን ከፊቱ አሳዶ ታላቅና አስፈሪ ታምራት እንዳደረገለትና ከግብፅም እንደ ተቤዠው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ማን አለ?

24. ሕዝብህን እስራኤልን ለዘላለሙ ያንተው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆነኸዋል።

25. “አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህና ለቤቱ የሰጠኸውን ተስፋ ለዘላለም ጠብቅለት፤ እንደተናገርኸውም ፈጽም፤

26. ስለዚህ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሆናል፤ ሰዎችም፣ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይላሉ። የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል።

27. “አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ‘እኔ ለአንተ ቤት እሠራልሃለሁ’ ብለህ ይህን ለባሪያህ ገልጸህለታል። ስለዚህ ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ በልቡ ደፈረ።

28. ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም የታመነ ነው፤ ይህንንም መልካም ነገር ለማድረግ ለባሪያህ ተስፋ ሰጥተኸዋል፤

29. በፊትህ ለዘላለም ጸንቶ እንዲኖር፣ አሁንም የባሪያህን ቤት እባክህ ባርክ። ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አንተው ራስህ ተናግረሃል፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘላለም ይባረካል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 7