ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 30:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. “ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘የግብፅ ተባባሪዎች ይወድቃሉ።የምትኵራራበት ብርታቷ ይወድቃል።ከሚግዶል እስከ አስዋን፣በውስጧ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

7. “ ‘በባድማ መሬቶች መካከል፣ባድማ ይሆናሉ፤ከተሞቻቸውም፣ከፈራረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ።

8. በግብፅ ላይ እሳት ስጭር፣ረዳቶቿ ሁሉ ሲደቁ፣በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ፤

9. “ ‘በዚያ ቀን ከእኔ ዘንድ መልእክተኞች በመርከብ ወጥተው ተዘልላ ከተቀመጠችበት ሁኔታ ለማውጣት ኢትዮጵያን ያስፈራሯታል፤ ግብፅ በጨለማ በምትዋጥበት ቀን ጭንቅ ይይዛቸዋል፤ ቀኑ በእርግጥ ይመጣልና።

10. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ፣ስፍር ቍጥር የሌለውን የግብፅን ሕዝብ እደመስሳለሁ።

11. ከአሕዛብ ሁሉ እጅግ ጨካኝ የሆኑት፣ እርሱና ሰራዊቱ፣ምድሪቱን ለማጥፋት እንዲመጡ ይደረጋል፤ሰይፋቸውን በግብፅ ላይ ይመዛሉ፤ምድሪቱንም ሬሳ በሬሳ ያደርጋሉ፤

12. የዐባይን ወንዝ ውሃ አደርቃለሁ፤ምድሪቱን ለክፉ ሰዎች እሸጣለሁ፤በባዕዳን እጅ፣ ምድሪቷንና በውስጧያለውን ሁሉ ባድማ አደርጋለሁ፤እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።

13. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ጣዖታትን አጠፋለሁ፤በሜምፊስ ያሉትን ምስሎች እደመስሳለሁ።ከእንግዲህ በግብፅ ገዥ አይኖርም፣በምድሪቱም ላይ ፍርሀት እሰዳለሁ።

14. ጳፕሮስን ባድማ አደርጋለሁ፤በጣኔዎስ ላይ እሳት እለኵሳለሁ፤በቴብስ ላይ ቅጣት አመጣለሁ።

15. የግብፅ ምሽግ በሆነችው፣በሲን ላይ መዓቴን አፈሳለሁ፤ስፍር ቍጥር የሌለውን የቴብስን ሕዝብ አጠፋለሁ።

16. በግብፅ ላይ እሳት አነዳለሁ፤ሲን በጭንቅ ትናጣለች፤ቴብስ በማዕበል ትወሰዳለች፤ሜምፊስ በማያቋርጥ ጭንቀት ውስጥ ትገባለች።

17. የሄልዮቱና የቡባስቱ ጐልማሶች፣በሰይፍ ይወድቃሉ፤ከተሞቹ ራሳቸውም ይማረካሉ።

18. የግብፅን ቀንበር በምሰብርበት ጊዜ፣በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል፤ከዚያም የተኵራራችበት ብርታት ይንኰታኰታል።በደመና ትሸፈናለች፤መንደሮቿም ይማረካሉ።

19. ስለዚህ በግብፅ ላይ ቅጣቴን አመጣለሁ፤እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 30