ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 119:108-122 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

108. እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈቅጄ ያቀረብሁትን የአፌን የምስጋና መሥዋዕት ተቀበል፤ሕግህንም አስተምረኝ።

109. ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤ሕግህን ግን አልረሳሁም።

110. ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤እኔ ግን መመሪያህን አልተላለፍሁም።

111. ምስክርነትህ የዘላለም ውርሴ ናት፤ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና።

112. ትእዛዝህን ለዘላለም፣ እስከ ወዲያኛው ለመፈጸም፣ልቤን ወደዚያው አዘነበልሁ።

113. መንታ ልብ ያላቸውን ጠላሁ፤ሕግህን ግን ወደድሁ።

114. አንተ መጠጊያዬና ጋሻዬ ነህ፤ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ።

115. የአምላኬን ትእዛዛት እጠብቅ ዘንድ፣እናንት ክፉ አድራጊዎች፣ ከእኔ ራቁ።

116. እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር።

117. ያለ ሥጋት እቀመጥ ዘንድ ደግፈህ ያዘኝ፤ሥርዐትህንም ዘወትር እመለከታለሁ።

118. መሰሪነታቸው በከንቱ ነውና፣ከሥርዐትህ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው።

119. የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፤ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ።

120. ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤ፍርድህንም እፈራለሁ።

121. ፍትሕና ጽድቅ ያለበትን ሠርቻለሁ፤ለሚጨቍኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ።

122. ለባሪያህ በጎነት ዋስትና ሁን፤እብሪተኛ እንዲጨቍነኝ አትፍቀድላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 119