ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 119:38-54 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

38. ትፈራ ዘንድ፣ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ፈጽም።

39. የምፈራውን መዋረድ ከእኔ አርቅ፤ደንብህ መልካም ነውና።

40. እነሆ፤ ድንጋጌህን ናፈቅሁ፤በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ።

41. እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ወደ እኔ ይምጣ፤ማዳንህም እንደ ቃልህ ይላክልኝ።

42. በቃልህ ታምኛለሁና፣ለሚሰድቡኝ መልስ እሰጣለሁ።

43. ሕግህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ።

44. ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ሕግህን ዘወትር እጠብቃለሁ።

45. ሥርዐትህን እሻለሁና፣እንደ ልቤ ወዲያ ወዲህ እመላለሳለሁ።

46. ምስክርነትህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ይህን በማድረግም ዕፍረት አይሰማኝም።

47. እኔ እወደዋለሁና፣በትእዛዝህ ደስ ይለኛል።

48. እጆቼን ወደምወዳቸው ትእዛዛትህ አነሣለሁ፤ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ።

49. ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ዐስብ፤በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና።

50. ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት።

51. እብሪተኞች እጅግ ተሣለቁብኝ፤እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም።

52. እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን ዐሰብሁ፤ በዚህም ተጽናናሁ።

53. ሕግህን ከተዉ ክፉዎች የተነሣ፣ቍጣ ወረረኝ።

54. በእንግድነቴ አገር፣ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 119