ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 119:73-87 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

73. እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ትእዛዛትህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ።

74. ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው።

75. እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደሆነ ዐወቅሁ።

76. ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ።

77. ሕግህ ደስታዬ ነውና፣በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ።

78. እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤እኔ ግን ትእዛዛትህን አሰላስላለሁ።

79. አንተን የሚፈሩህ፣ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ።

80. እኔ እንዳላፍር፤ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን።

81. ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።

82. “መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ።

83. ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣ሥርዐትህን አልረሳሁም።

84. የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው?ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን?

85. በሕግህ መሠረት የማይሄዱ፣እብሪተኞች ማጥመጃ ጒድጓድ ቈፈሩልኝ።

86. ትእዛዛትህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤ሰዎች ያለ ምክንያት አሳደውኛልና ርዳኝ።

87. ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 119