ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 119:81-94 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

81. ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።

82. “መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ።

83. ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣ሥርዐትህን አልረሳሁም።

84. የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው?ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን?

85. በሕግህ መሠረት የማይሄዱ፣እብሪተኞች ማጥመጃ ጒድጓድ ቈፈሩልኝ።

86. ትእዛዛትህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤ሰዎች ያለ ምክንያት አሳደውኛልና ርዳኝ።

87. ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም።

88. እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ።

89. እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

90. ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች።

91. ሁሉም አገልጋይህ ነውና፣በሕግህ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንተው ይኖራሉ።

92. ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣በመከራዬ ወቅት በጠፋሁ ነበር።

93. በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና፣ትእዛዝህን ከቶ አልረሳም።

94. እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤ሕግህንም ፈልጌአለሁና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 119