ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 119:92-109 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

92. ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣በመከራዬ ወቅት በጠፋሁ ነበር።

93. በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና፣ትእዛዝህን ከቶ አልረሳም።

94. እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤ሕግህንም ፈልጌአለሁና።

95. ክፉዎች ሊያጠፉኝ አድብተዋል፤እኔ ግን ምስክርነትህን አሰላስላለሁ።

96. ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ እንዳለው አየሁ፤ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።

97. አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።

98. ትእዛዛትህ ምንጊዜም ስለማይለዩኝ፣ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ።

99. ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ።

100. መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ።

101. ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ።

102. አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም።

103. ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው!ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው።

104. ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።

105. ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ለመንገዴም ብርሃን ነው።

106. የጽድቅ ሕግህን ለመጠበቅ፤ምያለሁ፤ ይህንኑ አጸናለሁ።

107. እጅግ ተቸግሬአለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።

108. እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈቅጄ ያቀረብሁትን የአፌን የምስጋና መሥዋዕት ተቀበል፤ሕግህንም አስተምረኝ።

109. ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤ሕግህን ግን አልረሳሁም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 119