ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 139:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ደግሞም ዐወቅኸኝ።

2. አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ።

3. መሄድ መተኛቴን አጥርተህ ታውቃለህ፤መንገዶቼንም ሁሉ ተረድተሃቸዋል።

4. እግዚአብሔር ሆይ፤ ገና ቃል ከአንደበቴ ሳይወጣ፣እነሆ፤ አንተ ሁሉንም ታውቃለህ።

5. አንተ ከኋላም ከፊትም ዙሪያዬን ከለልኸኝ፤እጅህንም በላዬ አደረግህ።

6. እንዲህ ያለው ዕውቀት ለኔ ድንቅ ነው፤ልደርስበትም የማልችል ከፍ ያለ ነው።

7. ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ?ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?

8. ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ አለህ፤መኝታዬንም በሲኦል ባደርግ በዚያ ትገኛለህ።

9. በንጋት ክንፍ ተነሥቼ ብበር፣እስከ ባሕሩ ዳርቻ መጨረሻ ብሄድ፣

10. በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች፤ቀኝ እጅህም አጥብቃ ትይዘኛለች።

11. እኔም፣ “ጨለማው በርግጥ ይሰውረኛል፤በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ይሆናል” ብል፣

12. ጨለማ የአንተን ዐይን አይዝም፤ሌሊቱም እንደ ቀን ያበራል፤ጨለማም ብርሃንም ለአንተ አንድ ናቸውና።

13. አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 139