ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 37:19-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. በክፉ ጊዜ ዐንገት አይደፉም፤በራብ ዘመንም ይጠግባሉ።

20. ክፉዎች ግን ይጠፋሉ፤ የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደ መስክ ውበት ይሆናሉ፤ይጠፋሉ፤ እንደ ጢስም ተነው ይጠፋሉ።

21. ኀጢአተኛ ይበደራል፤ መልሶም አይከፍልም፤ጻድቅ ግን ይቸራል።

22. እግዚአብሔር የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤እርሱ የሚረግማቸው ግን ይጠፋሉ።

23. የሰው አካሄድ በእግዚአብሔር ይጸናል፤በመንገዱ ደስ ይለዋል።

24. ቢሰናከልም አይወድቅም፤ እግዚአብሔር በእጁ ደግፎ ይይዘዋልና።

25. ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም።

26. ሁል ጊዜ ቸር ነው፤ ያበድራልም፤ልጆቹም የተባረኩ ይሆናሉ።

27. ከክፉ ራቅ፤ መልካሙንም አድርግ፤ለዘላለምም ትኖራለህ።

28. እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳልና፤ታማኞቹንም አይጥልም፤ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፤የኀጢአተኛው ዘር ግን ይጠፋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 37