ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 37:3-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ።

4. በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።

5. መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል፤

6. ጽድቅህን እንደ ብርሃን፣ያንተን ፍትሕ እንደ ቀትር ፀሓይ ያበራዋል።

7. በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤መንገዱ በተቃናለት፣ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር።

8. ከንዴት ተቈጠብ፤ ቍጣንም ተወው፤ወደ እኵይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ።

9. ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ።

10. ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም።

11. ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።

12. ክፉዎች በጻድቃን ላይ ያሤራሉ፤ጥርሳቸውንም ያፋጩባቸዋል።

13. እግዚአብሔር ግን ይሥቅባቸዋል፤ቀናቸው እንደ ደረሰ ያውቃልና።

14. ድኾችንና ችግረኞችን ለመጣል፣አካሄዳቸው ቀና የሆነውንም ለመግደል፣ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፤ቀስታቸውንም ገተሩ።

15. ሰይፋቸው የገዛ ልባቸውን ይወጋል፤ቀስታቸውም ይሰበራል።

16. የጻድቅ ጥቂት ሀብት፣ከክፉዎች ብዙ ጥሪት ይበልጣል።

17. የክፉዎች ክንድ ይሰበራልና፤ጻድቃንን ግን እግዚአብሔር ደግፎ ይይዛቸዋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 37