ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አሞጽ 9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እስራኤል ትጠፋለች

1. ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ፤“መድረኮቹ እንዲናወጡ፣ጒልላቶቹን ምታ፣በሕዝቡም ሁሉ ራስ ላይ ሰባብራቸው፤የቀሩትን በሰይፍ እገድላቸዋለሁ፤ከእነርሱ አንድም ሰው አይሸሽም፤ቢሸሽም የሚያመልጥ የለም።

2. መቃብር በጥልቀት ቈፍረው ቢወርዱም፣እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ወደ ሰማይ ቢወጡም፣ከዚያ አወርዳቸዋለሁ።

3. በቀርሜሎስ ጫፍ ላይ ቢሸሸጉም፣አድኜ ፈልጌ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤እይዛቸዋለሁም፤በጥልቅ ባሕር ውስጥ ከእኔ ቢሸሸጉም፣በዚያ እባቡ እንዲነድፋቸው አዘዋለሁ፤

4. በጠላቶቻቸው ተነድተው ለምርኮ ቢወሰዱም፣በዚያ እንዲገድላቸው ሰይፍን አዛለሁ፤ለመልካም ሳይሆን ለክፉ፣ዓይኔን በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ።

5. ጌታ፣ እግዚአብሔር ጸባኦት፣ምድርን ይዳስሳል፤እርሷም ትቀልጣለች፤በውስጥዋ የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤የምድር ሁለመና እንደ ዐባይ ወንዝ ይነሣል፤እንደ ግብጽ ወንዝም ይወርዳል።

6. መኖሪያውን በሰማይ የሚሠራ፣መሠረቱንም በምድር የሚያደርግ፣የባሕርን ውሃ የሚጠራ፣በምድርም ገጽ ላይ የሚያፈስ፣እርሱ ስሙ እግዚአብሔር ነው።

7. “እናንት እስራኤላውያን፣ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን?”ይላል እግዚአብሔር“እስራኤልን ከግብጽ፣ፍልስጥኤማውያንን ከከፍቶር፣ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?

8. “እነሆ፤ የጌታ እግዚአብሔር ዐይኖች፣በኀጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፤ከምድር ገጽ፣ ፈጽሜ አጠፋዋለሁ፤የያዕቆብን ቤት ግን፣ ሙሉ በሙሉአልደመስስም፤”ይላል እግዚአብሔር።

9. “እነሆ፤ ትእዛዝ እሰጣለሁ፤እህል በወንፊት እንደሚነፋ፣የእስራኤልን ቤት፣በሕዝብ ሁሉ መካከል እንዲሁ አደርጋለሁ፤ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም።

10. በሕዝቤ መካከል ያሉ፣‘ክፉ ነገር አያገኘንም ወይም አይደርስብንም’ የሚሉ፣ኀጢአተኞች ሁሉ፣በሰይፍ ይሞታሉ።

የእስራኤል መመለስ

11. “በዚያ ቀን፣የወደቀውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፤የተሰበረውን እጠግናለሁ፤የፈረሰውን ዐድሳለሁ፤ቀድሞ እንደነበረም አድርጌ እሠራዋለሁ፤

12. ስለዚህ የኤዶምን ትሩፍ፣በስሜ የተጠሩትንም ሕዝቦች ሁሉ ይወርሳሉ፤”ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር።

13. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ ዐጫጁ ዐጭዶ ሳይጨርስ፣ዐራሹ በላዩ የሚደርስበት፣ችግኝ ተካዩም ገና ተክሎ ሳይጨርስ፣ወይን ጨማቂው የሚደርስበት ጊዜ ይመጣል፤አዲስ የወይን ጠጅ ከተራሮች ይንጠባጠባል፤ከኰረብቶችም ሁሉ ይፈሳል።

14. የተሰደደውን ሕዝቤን እስራኤልን እመልሳለሁ፤እነርሱም የፈራረሱትን ከተሞች መልሰው ሠርተው በውስጣቸው ይኖራሉ።የወይን ተክል ተክለው፣ ጠጁን ይጠጣሉ፤አትክልት ተክለው ፍሬውን ይበላሉ።

15. እስራኤልን በገዛ ምድራቸው እተክላቸዋለሁ፤ከሰጠኋቸውም ምድር፣ ዳግመኛአይነቀሉም”ይላል አምላክህ እግዚአብሔር።