ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የቀሪው ምድር መከፋፈል

1. መላው የእስራኤላውያን ማኅበር በሴሎ ተሰበሰቡ፣ የመገናኛውንም ድንኳን እዚያው ተከሉ፤ ምድሪቱም ጸጥ ብላ ተገዛችላቸው።

2. ዳሩ ግን ርስት ገና ያልተሰጣቸው ሰባት የእስራኤል ነገዶች ነበሩ።

3. ስለዚህ ኢያሱ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፤ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ለመውረስ ቸል የምትሉት እስከ መቼ ነው?

4. አሁንም ከእያንዳንዱ ነገድ ሦስት ሦስት ሰው ምረጡ፤ እኔም ምድሪቱን ተዘዋውረው እንዲያጠኑና እያንዳንዱም ነገድ መውረስ የሚገባውን ድርሻ ዝርዝር መግለጫ ጽፈው እንዲያመጡ እልካቸዋለሁ፤ ከዚያም ወደ እኔ ይመለሳሉ።

5. ምድሪቱንም ሰባት ቦታ ይከፍሏታል፤ ይሁዳ በደቡብ፣ የዮሴፍ ዘሮች በሰሜን በኩል የተመደበላቸውን ርስት ይዘው ይኖራሉ።

6. የሰባቱን የመሬት ክፍፍል ዝርዝር መግለጫ ጽፋችሁ ወደኔ ታመጡና በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ እጥልላችኋለሁ።

7. ሌዋውያኑ ግን ለእግዚአብሔር የሚሰጡት የክህነት አገልግሎት ርስታቸው ስለ ሆነ በእናንተ መካከል ድርሻ አይኖራቸውም፤ ጋድ፣ ሮቤልና የምናሴ ነገድ እኩሌታም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምሥራቅ ዮርዳኖስ የሰጣቸውን ርስት ቀደም አድርገው ወስደዋል።”

8. ሰዎቹ የምድሪቱን ሁኔታ ለማጥናትና ለመመዝገብ ጒዞ ሲጀምሩ ኢያሱ፣ “ሄዳችሁ የምድሪቱን ሁኔታ አጥኑና በዝርዝር ከጻፋችሁ በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም እዚሁ ሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ እጥልላችኋለሁ” አላቸው።

9. ስለዚህም ሰዎቹ ሄደው ምድሪቱን ተዘዋውረው አዩ፤ ከነከተሞቿም ሰባት ቦታ ከፍለው በጥቅልል ብራና ላይ በዝርዝር ጻፉ፤ ከዚያም በሴሎ ሰፈር ወዳለው ወደ ኢያሱ ተመለሱ።

10. ኢያሱም በሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ ጣለላቸው፤ ምድሪቱንም እንደየነገዱ ደልድሎ ለእስራኤላውያን አከፋፈላቸው።

ለብንያም ነገድ የተመደበው ድርሻ

11. ለብንያም ነገድ የሆነው የመጀመሪያው ዕጣ በየጐሣ በየጐሣው ወጣ፤ በዕጣ የደረሳቸውም ምድር የሚገኘው በይሁዳና በዮሴፍ ነገዶች ርስት መካከል ሲሆን እንደሚከተለው ነው፤

12. በሰሜን ያለው ድንበራቸው ከዮርዳኖስ ይነሣና የኢያሪኮን ሰሜናዊ ተረተር አልፎ፣ በስተ ምዕራብ ወዳለው ኰረብታማ ምድር በማምራት፣ እስከ ቤትአዌን ምድረ በዳ ይዘልቃል።

13. ከዚያ ደግሞ ወደ ደቡብ ሎዛ ማለት ወደ ቤቴል ተረተር ይሻገርና በታችኛው ቤትሖሮን በስተ ደቡብ ባለው ተራራ በኩል አድርጎ ወደ አጣሮት አዳር ይወርዳል።

14. በስተ ደቡብ ያለው ድንበር ከቤትሖሮን ትይዩ ካለው ኰረብታ ተነሥቶ፣ በምዕራብ በኩል ወደ ደቡብ በመታጠፍ፣ የይሁዳ ነገድ ከተማ ወደሆነችው ወደ ቂርያትበኣል ማለት ወደ ቂርያትይዓሪም ያልፋል፤ ይህ እንግዲህ በምዕራብ በኩል ያለው ድንበር ነው።

15. በስተ ደቡብ ያለው ድንበር ደግሞ በምዕራብ በኩል ከቂርያትይዓሪም ጥግ ይነሣና እስከ ነፍቶ ውሃ ምንጭ ይዘልቃል፤

16. ይኸው ድንበር ከራፋይም ሸለቆ በስተ ሰሜን ባለው በሄኖም ሸለቆ ትይዩ ቊልቊል ወደ ኰረብታው ግርጌ ይወርዳል፤ ከዚያም ከኢያቡሳውያን ከተማ በደቡብ በኩል ባለው ተረተር አድርጎ ወደ ሄኖም ሸለቆ በመውረድ እስከ ዓይንሮጌል ይዘልቃል።

17. ደግሞም ወደ ሰሜን ይታጠፍና በቤትሳሚስ በኩል አድርጎ እስከ ጌሊሎት ይዘልቃል፤ ከዚያም በአዱሚም መተላለፊያ ትይዩ እስካለው እስከ ሮቤል ልጅ እስከ ቦሀን ድንጋይ ይወርዳል።

18. ወደ ቤትዓረባ ሰሜናዊ ተረተር በመቀጠል ቊልቊል ወደ ዐረባ ይወርዳል።

19. ከዚያም ሰሜናዊን የቤትሖግላንን ተረተር አልፎ ይሄድና በስተ ደቡብ የዮርዳኖስ ወንዝ እስከሚገባበት እስከ ሙት የባሕር ወሽመጥ ይዘልቃል፤ ይህም ደቡባዊ ድንበሩ ነው።

20. በምሥራቅ በኩል ያለው ድንበር፣ ራሱ የዮርዳኖስ ወንዝ ነው።ይህ እንግዲህ የብንያም ነገድ ጐሣዎች በርስትነት የወረሷት ምድር ዳር ድንበሮቿ ሁሉ እነዚህ ነበሩ።

21. የብንያም ነገድ በየጐሣቸው የያዟቸው ከተሞች እነዚህ ናቸው፤ ኢያሪኮ፣ ቤትሖግላ፣ ዓመቀጺጽ፣

22. ቤትዓረባ፣ ዘማራይም፣ ቤቴል፣

23. ዓዊም፣ ፋራ፣ ኤፍራታ፣

24. ክፊርዓሞናይ፣ ዖፍኒ እንዲሁም ጋባ ናቸው፤ እነዚህም ከነ መንደሮቻቸው ዐሥራ ሁለት ከተሞች ናቸው።

25. ገባዖን፣ ራማ፣ ብኤሮት፣

26. ምጽጳ፣ ከፊራ፣ አሞቂ፣

27. ሬቄም፣ ይርጵኤል፣ ተርአላ፣

28. ጼላ፣ ኤሌፍ፣ የኢያቡሳውያን ከተማ ኢየሩሳሌም፣ ጊብዓ እንዲሁም ቂርያት ነበሩ፤ እነዚህም ከነ መንደሮቻቸው ዐሥራ አራት ከተሞች ናቸው።እንግዲህ የብንያም ነገድ በየጐሣቸው የወረሱት ይህ ነበር።