ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢያሱ ለመሪዎች የተናገረው የመሰናበቻ ቃል

1. እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፋቸው እነሆ፣ ብዙ ዘመን አለፈ፤ በዚህ ጊዜ ኢያሱ በጣም አርጅቶ፣ ዕድሜውም ገፍቶ ነበር፤

2. ኢያሱ እስራኤልን ሁሉ አለቆቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ፈራጆቻቸውንና ሹማምታቸውን በሙሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ አርጅቻለሁ፤ ዕድሜዬም ገፍቶአል።

3. አምላካችሁ እግዚአብሔር ስለ እናንተ ሲል በእነዚህ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረገውን ማናቸውንም ነገር እናንተው ራሳችሁ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋላችሁ ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው።

4. ከዮርዳኖስ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ በሙሉ ካሸነፍኋቸው ሕዝቦች ያልወረሳችሁትን ቀሪ ምድር ርስት እንዲሆን ለየነገዶቻችሁ እንዴት አድርጌ በዕጣ እንዳከፋፈልኋችሁ አስታውሱ።

5. ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ከፊታችሁም ያሉበትን ስፍራ ያስለቅቃቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁም ተስፋ መሠረት ምድራቸውን ትወርሳላችሁ።

6. “በርቱ፤ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳትሉ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ እጅግ በርቱ።

7. በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር አትተባበሩ፤ የአማልክቶቻቸውን ስም አትጥሩ፤ አትማሉባቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትስገዱላቸውም፤

8. ነገር ግን እስካሁን እንዳደረጋችሁት ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አጥብቃችሁ ያዙ።

9. “እግዚአብሔር ታላላቅና ኀያላን ሕዝቦችን ከፊታችሁ አሳድዶ አስወጥቶአቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም።

10. አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት የሚዋጋላችሁ ስለ ሆነ፣ ከእናንተ አንዱ ሰው ሺውን ያሳድዳል።

11. ስለዚህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለመውደድ ተጠንቀቁ።

12. ነገር ግን ከእርሱ ተመልሳችሁ ተርፈው በመካከላችሁ ከሚገኙት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ብትተባበሩ፣ በጋብቻም ብትተሳሰሩና ብትቀላቀሉ፣

13. አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ከፊታችሁ እንደማያወጣቸው ይህን ልታውቁ ይገባል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር እስክትጠፉ ድረስም ወጥመድና አሽክላ፣ ለጀርባችሁ ጅራፍ፣ ለዐይኖቻችሁም እሾኽ ይሆኑባችኋል።

14. “እነሆ፤ አሁን የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።

15. ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁ መልካሙ ተስፋ በሙሉ እንደ ተፈጸመ ሁሉ፣ እንደዚሁም አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር እስኪያጠፋችሁ ድረስ ክፉውን ነገር ያመጣባችኋል።

16. አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ኪዳን ብታፈርሱ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብትሰግዱላቸው የእግዚአብሔር ቊጣ በላያችሁ ይነዳል፤ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”