ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 21:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ለሜራሪ ዝርያዎች በየጐሣቸው ከሮቤል፣ ከጋድና ከዛብሎን ነገዶች ዐሥር ከተሞች ተመደቡላቸው።

8. ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ባዘዘው መሠረት፣ እነዚህን ከተሞችና መሰማሪያቸውን ለሌዋውያኑ በዕጣ መደቡላቸው።

9. ከይሁዳና ከስምዖን ነገዶች ደግሞ ከዚህ በታች በስም የተጠቀሱትን ከተሞች በዕጣ መደቡላቸው።

10. እነዚህም ከተሞች የሌዊ ልጆች፣ የቀዓት ጐሣዎች ለሆኑት ለአሮን ዝርያዎች ተመደቡ፤ ይህም የሆነው የመጀመሪያው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣላቸው ነበር፤

11. እነርሱም በተራራማው የይሁዳ ምድር ያለችውን ኬብሮን የተባለችውን ቂርያት አርባቅን በዙሪያዋ ካለው መሰማሪያ ጋር ሰጧቸው፤ አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ።

12. ይሁን እንጂ በከተማዪቱ ዙሪያ ያሉትን ዕርሻዎችና መንደሮች ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርገው ሰጡት።

13. እንደዚሁም ለነፍስ ገዳይ መማጠኛ የሆነችውን ኬብሮንንና ልብናን ከነ ማሰማሪያቸው ለካህኑ ለአሮን ልጆች ሰጧቸው፤

14. ደግሞም የቲርን፣ ኤሽትሞዓን፣

15. ሖሎንን፣ ዳቤርን፣

16. ዐይንን፣ ዮጣንና ቤትሳሚስን ከነ ማሰማሪያቸው ሰጧቸው፤ እነዚህ ዘጠኙ ከተሞች ከሁሉ ነገዶች ይዞታ ላይ ተከፍለው የተሰጡ ናቸው።

17. ከብንያም ነገድ ገባዖን፣ ጌባዕ፣

18. ዓናቶትና አልሞን የተባሉትን አራት ከተሞች ከነ ማሰማሪያዎቻቸው ሰጧቸው።

19. ለካህናቱ ለአሮን ዝርያዎች ከነ ማሰማሪያቸው የተሰጧቸው ከተሞች ዐሥራ ሦስት ነበሩ።

20. የሌዊ ልጅ የቀዓት ጐሣዎች ለሆኑት ለሌሎቹ ደግሞ ከኤፍሬም ነገድ ላይ ተከፍለው የሚከተሉት ከተሞች በዕጣ ተመደቡላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 21