ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 22:4-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እነዚህን ትእዛዛት በሚገባ ብትጠብቁ፣ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታት፣ ከመኳንንታቸውና ከሕዝባቸው ጋር በሠረገሎችና በፈረሶች ተቀምጠው በዚህ ቤተ መንግሥት በሮች ይገባሉ፤ ይወጣሉም።

5. ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት ባትጠብቁ፣ ይህ ቤተ መንግሥት እንዲወድም በራሴ ምያለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ”

6. ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት እንዲህ ይላል፤“አንተ ለእኔ እንደ ገለዓድ፣እንደ ሊባኖስ ተራራ ጫፍ ውብ ብትሆንም፣በርግጥ እንደ ምድረ በዳ፣ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች አደርግሃለሁ።

7. በነፍስ ወከፍ መሣሪያ የሚይዙትን፣አጥፊዎችን በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ።ምርጥ የዝግባ ዛፎችን ይቈርጣሉ፤ወደ እሳትም ይጥሏቸዋል።

8. “ከተለያየ አገር የመጡ ሕዝቦች በዚህች ከተማ በኩል ሲያልፉ፣ ‘እግዚአብሔር በዚህች ታላቅ ከተማ ላይ ለምን እንዲህ አደረገ?’ እያሉ እርስ በርስ ይነጋገራሉ፤

9. ከዚያም፣ ‘የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ኪዳን ትተው ሌሎችን አማልክት ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው’ ይላሉ።”

10. ከእንግዲህ ስለማይመለስ፣የተወለደባትንም ምድር ዳግመኛ ስለማያይ፣ለተማረከው ንጉሥ አምርራችሁ አልቅሱ እንጂ፣ቀድሞ ለሞተው አታልቅሱ፤ አትዘኑም።

11. በአባቱ ምትክ በይሁዳ ላይ ስለ ነገሠው፣ ከዚህ ስፍራ በምርኮ ስለ ተወሰደው፣ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “ከእንግዲህ አይመለስም፤

12. ተማርኮ በሄደበት አገር ይሞታል እንጂ ይህቺን ምድር ዳግመኛ አያይም።”

13. “ቤተ መንግሥቱን በግፍ ለሚሠራ፣ሰገነቱንም ፍትሕ በማዛባት ለሚገነባ፣ወገኑን በነጻ ለሚያሠራ፣የድካሙንም ዋጋ ለማይከፍለው፣

14. ‘ባለ ትልልቅ ሰገነት፣ሰፊ ቤተ መንግሥት ለራሴ እሠራለሁ’ ለሚል ወዮለት!ሰፋፊ መስኮቶችን ያበጅለታል፤በዝግባ እንጨት ያስጌጠዋል፤ቀይ ቀለምም ይቀባዋል።

15. “በዝግባ ዕንጨት ብዛት፣የነገሥህ ይመስልሃልን?አባትህስ ፍትሕንና ጽድቅን በማድረጉ፣የሚበላውና የሚጠጣው ጐድሎት ነበርን?እነሆ፣ ሁሉም መልካም ሆነለት።

16. የድኾችንና የችግረኞችን ፍትሕ አላጓደለም፤ስለዚህም ሁሉ መልካም ሆነለት።እኔን ማወቅ ማለት ይህ አይደለምን?”ይላል እግዚአብሔር።

17. “የአንተ ዐይንና ልብ ያረፉት ግን፣አጭበርብሮ ጥቅምን በማግኘት፣የንጹሑን ደም በማፍሰስ፣ጭቈናንና ግፍን በመሥራት ላይ ብቻ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 22