ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 6:11-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ደግሞም ይህን ትእዛዝ የሚለውጥ ማንም ሰው ቢኖር፣ ከቤቱ ምሰሶ ተነቅሎ በምሰሶው ላይ እንዲሰቀል፣ ስለ ወንጀሉም ቤቱ የቈሻሻ መጣያ እንዲሆን አዝዣለሁ።

12. ይህን ትእዛዝ ለማፍረስ ወይም በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ለማጥፋት እጁን የሚያነሣ ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ፣ ስሙን በዚያ እንዲኖር ያደረገ አምላክ ያጥፋው።እኔ ዳርዮስ በትጋት እንዲፈጸም ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።

13. ከዚያም ንጉሡ ዳርዮስ ባዘዘው መሠረት በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ሥራው በትጋት እንዲፈጸም አደረጉ።

14. ስለዚህ የአይሁድ መሪዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተጽናኑ ሥራውን ቀጠሉ፤ የቤተ መቅደሱንም ሥራ በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ እንዲሁም የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፣ ዳርዮስና አርጤክስስ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት ሠርተው ጨረሱ።

15. ይህም ቤተ መቅደስ ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር በሦስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።

16. ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና የቀሩትም ምርኮኞች የእግዚአብሔርን ቤት ምረቃ በዓል በደስታ አከበሩ።

17. ለዚህ ለእግዚአብሔር ቤት ምረቃም አንድ መቶ ወይፈኖችን፣ ሁለት መቶ አውራ በጎችንና አራት መቶ ተባዕት ጠቦቶችን ሰጡ፤ ለመላው እስራኤል የኀጢአት መሥዋዕትም ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ልክ አቀረቡ።

18. በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር አገልግሎት ካህናቱን በየማዕረጋቸው፣ ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው መደቧቸው።

19. ምርኮኞቹ በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል አከበሩ።

20. ካህናቱና ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ፤ ሁሉም በሥርዐቱ መሠረት ነጽተው ነበር። ሌዋውያኑም የፋሲካውን በግ ለምርኮኞቹ ሁሉ፣ ለካህናት ወንድሞቻቸውና ለራሳቸው ዐረዱ።

21. ስለዚህ ከምርኮ የተመለሱት እስራኤላውያን የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በአምልኮ ይፈልጉት ዘንድ ራሳቸውን ከአረማውያን ጎረቤቶቻቸው ርኵሰት ከለዩት ሁሉ ጋር በሉ።

22. እግዚአብሔር ደስ እንዲሰኙ ስላደረጋቸው የቂጣን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አከበሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ልብ ለውጦ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ቤት ሥራ እንዲያግዛቸው አድርጎ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 6