ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 14:9-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ብቻ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለንና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩአቸው። ጥላቸው ተገፎአል፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከእኛ ጋር ነውና አትፍሯቸው።”

10. መላው ማኅበር ግን በድንጋይ ሊወግሯቸው ተነጋገሩ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር በመገናኛው ድንኳን ለእስራኤላውያን ሁሉ ተገለጠ።

11. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል” እነዚህን ሁሉ ታምራት በመካከሉ እያደረግሁ የማያምንብኝስ እስከ መቼ ነው?

12. በቸነፈር እመታዋለሁ፤ እደመስሰዋለሁም፤ አንተን ግን ብርቱና ታላቅ ለሆነ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”

13. ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ነገሩን ግብፃውያን ቢሰሙትስ! ይህን ሕዝብ በኀይልህ ከመካከላቸው አውጥተኸዋልና፤

14. የተደረገውንም በዚች ምድር ለሚኖሩት ሰዎች ይነግሯቸዋል። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፣ አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋር መሆንህን፣ ደግሞም አንተ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ፊት ለፊት እንደታየህና ደመናህ በላያቸው እንደሆነ፣ አንተም ቀን በደመና ዐምድ ሌሊትም በእሳት ዐምድ እፊት እፊታቸው እየሄድህ እንደ መራሃቸው ቀድሞውኑ ሰምተዋል።

15. ታዲያ ይህን ሁሉ ሕዝብ በአንድ ጊዜ ብትፈጀው ዝናህን የሰሙ ሕዝቦች፣

16. ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ለዚህ ሕዝብ ይሰጠው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባለት ምድር ሊያስገባው ባለመቻሉ በምድረ በዳ ፈጀው’ ይሉሃል።

17. “አሁንም እንዲህ ስትል በተናገርኸው መሠረት የጌታ ኀይል ይገለጥ፤

18. ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩ የበዛ፣ ኀጢአትንና ዐመፃን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ የማይተው፣ ስለ አባቶቻቸውም ኀጢአት ልጆችን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ የሚቀጣ ነው።’

19. ከግብፅ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው ሁሉ እንደ ፍቅርህ ታላቅነት መጠን እባክህ አሁንም የዚህን ሕዝብ ኀጢአት ይቅር በል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 14