ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 29:8-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ሁሉም እንከን የሌለባቸው አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።

9. ከወይፈኑ ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከአውራ በጉ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ በዘይት የተለወሰ ዱቄት አቅርቡ፤

10. ከሰባቱ የበግ ጠቦቶችም ከእያንዳንዳቸው ጋር በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ።

11. ማስተስረያ እንዲሆንም ለኀጢአት መሥዋዕት ከሚቀርበው እንዲሁም ከእህሉ ቊርባንና ከመጠጡ ቊርባን ጋር በመደበኛነት ቀርቦ ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

12. “ ‘በሰባተኛው ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ሥራ አትሥሩ፤ ለእግዚአብሔርም (ያህዌ) የሰባት ቀን በዓል አክብሩ።

13. ሁሉም እንከን የሌለባቸው ዐሥራ ሦስት ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ እንዲያሰኝ በእሳት አቅርቡ

14. ከዐሥራ ሦስቱ ወይፈኖች ከእያንዳንዳቸው ጋር የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከሁለቱ አውራ በጎችም ከእያንዳንዳቸው ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የእህል ቊርባን አቅርቡ፤

15. እንዲሁም ከዐሥራ አራቱ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋር የኢፍ አንድ ዐሥረኛ በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የእህል ቊርባን አቅርቡ።

16. ከእህሉ ቊርባንና ከመጠጡ ቊርባን ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

17. “ ‘በሁለተኛው ቀን ሁሉም እንከን የሌለባቸው ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ።

18. ከወይፈኖቹ፣ ከአውራ በጎቹና ከበግ ጠቦቶቹ ጋር በተወሰነው ቊጥር መሠረት የእህል ቊርባናቸውንና የመጠጥ ቊርባናቸውን አብራችሁ አቅርቡ።

19. ደግሞም ከእህሉ ቊርባንና ከመጠጡ ቊርባን ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ አውራ ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

20. “ ‘በሦስተኛው ቀን ሁሉም እንከን የሌለባቸው ዐሥራ አንድ ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ።

21. ከወይፈኖቹ፣ ከአውራ በጎቹና ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የእህል ቊርባናቸውንና የመጠጥ ቊርባናቸውን በተወሰነው ቊጥር መሠረት አብራችሁ አቅርቡ።

22. ደግሞም ከእህሉ ቊርባኑና ከመጠጡ ቍርባን ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

23. “ ‘በአራተኛው ቀን ሁሉም እንከን የሌለባቸው ዐሥር ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ።

24. ከወይፈኖቹ፣ ከአውራ በጎቹና ከጠቦቶቹ ጋር የእህል ቊርባናቸውንና የመጠጥ ቊርባናቸውን በተደነገገው ቊጥር መሠረት አቅርቡ።

25. ደግሞም ከእህሉ ቊርባኑና ከመጠጡ ቊርባን ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

26. “ ‘በአምስተኛው ቀን ሁሉም እንከን የሌለባቸው ዘጠኝ ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 29