ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘካርያስ 8:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እንደ ገናም የእግዚአብሔር ጸባኦት ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2. እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “ስለ ጽዮን እጅግ ቀንቻለሁ፤ ስለ እርሷም በቅናት ነድጃለሁ።

3. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ወደ ጽዮን እመለሳለሁ፤ በኢየሩሳሌም እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የእግዚአብሔር ጸባኦት ተራራም ቅዱስ ተራራ ይባላል።”

4. እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “ሽማግሌዎችና አሮጊቶች እንደ ገና በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፤ እያንዳንዳቸውም ከዕድሜአቸው ብዛት የተነሣ ምርኵዝ ይይዛሉ።

5. የከተማዪቱም አደባባዮች እዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።”

6. እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “በዚያን ጊዜ ይህ ለቀረው የእስራኤል ሕዝብ አስደናቂ መስሎ ሊታይ ይችላል፤ ለእኔ ግን አስደናቂ ሊሆን ይችላልን?” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

7. እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤን ከምሥራቅና ከምዕራብ አገር እታደጋለሁ።

8. በኢየሩሳሌም እንዲኖሩ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም በጽድቅና በታማኝነት አምላካቸው እሆናለሁ።”

9. እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “የእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት መሠረት ሲጣል፣ በዚያ የነበሩ ነቢያት የተናገሩትን ቃል አሁን የምትሰሙ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት እጃችሁን አበርቱ።

10. ከዚያ በፊት ለሰው ደመወዝ፣ ለእንስሳም ኪራይ አይከፈልም ነበር፤ ጠላት በመኖሩም ማንም ሥራውን በሰላም ማከናወን አልቻለም፤ እያንዳንዱ ሰው በባልንጀራው ላይ እንዲነሣ አድርጌ ነበርና።

11. አሁን ግን ቀድሞ እንዳደረግሁት በዚህ በቀረው ሕዝብ ላይ አላደርግም” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

12. “ዘሩ ጥሩ ሆኖ ይበቅላል፤ ወይኑ ፍሬውን ያፈራል፤ ምድሪቱ አዝመራዋን ታበረክታለች፤ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ለቀሪው ሕዝብ ርስት አድርጌ እሰጣለሁ።

13. የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በአሕዛብ መካከል የርግማን ምሳሌ ነበራችሁ፤ አሁን ግን አድናችኋለሁ፤ እናንተም በረከት ትሆናላችሁ። አትፍሩ፤ ነገር ግን እጃችሁን አበርቱ።”

14. እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ ባስቈጡኝ ጊዜ ያላንዳች ሐዘኔታ ጥፋት ላመጣባችሁ እንደ ወሰንሁ፣” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤

15. “አሁን ደግሞ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ መልካም ነገርን ላደርግ ወስኛለሁ፤ አትፍሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘካርያስ 8