ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 38:18-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. “ታዲያ ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርሷም፣ “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያው፣ እንደዚሁም ይህን በትርህን ስጠኝ” አለችው። የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና አብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች።

19. ከዚያም ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ፣ ሻሽዋን አውልቃ እንደ ወትሮዋ የመበለት ልብሷን ለበሰች።

20. ይሁዳ በመያዣ ስም የሰጣትን ዕቃዎች ለማስመለስ የፍየሉን ጠቦት በዓዶሎማዊ ወዳጁ እጅ ላከላት፣ መልእክተኛው ግን ሴትየዋን ሊያገኛት አልቻለም።

21. “በኤናይም ከተማ መግቢያ ከመንገዱ ዳር የነበረች ያቺ ዝሙት ዐዳሪ የት ደረሰች?” ሲል ጠየቃቸው። ሰዎቹም፣ “በዚህ አካባቢ ኧረ ምንም ዝሙት ዐዳሪ ታይታ አትታወቅም” አሉት።

22. መልእክተኛውም ወደ ይሁዳ ተመልሶ፣ “ሴቲቱን ላገኛት አልቻልኩም፤ ነዋሪዎቹም ‘በዚህ አካባቢ እንደዚህች ያለች ዝሙት ዐዳሪ የለችም’ አሉኝ” ብሎ ነገረው።

23. ይሁዳም፣ “እንግዲህ መያዣውን እንደ ያዘች ትቅር፤ አለዚያ መሣቂያ እንሆናለን። ለነገሩማ ይህን ፍየል ላክሁ፤ አንተም ፈልገህ አላገኘሃትም” አለ።

24. ከሦስት ወር ያህል በኋላ፣ “ምራትህ ትዕማር ዘማዊ ሆናለች፤ ከዚህም የተነሣ አርግዛለች” ተብሎ ለይሁዳ ተነገረው።ይሁዳም፣ “አውጧትና በእሳት ተቃጥላ ትሙት” አለ።

25. እርሷም ተይዛ በምትወሰድበት ጊዜ ለዐማትዋ፣ “እኔ ያረገዝሁት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው” ስትል ላከችበት፤ ደግሞም፣ “የማኅተሙ ቀለበት ከነማንጠልጠያውና በትሩ የማን እንደሆነ እስቲ ተመልከት” አለችው።

26. ይሁዳም ዕቃዎቹን ዐውቆ፣ “ልጄ ሴሎም እንዲያገባት ባለማድረጌ፣ እርሷ ከእኔ ይልቅ ትክክል ናት” አለ። ከዚያም በኋላ ከእርሷ ጋር አልተኛም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 38