ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 41:48-57 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

48. በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመታት፣ ዮሴፍ በግብፅ አገር የተገኘውን ምርት ሰብስቦ በየከተሞቹ አከማቸ፤ በእያንዳንዱ ከተማ ከየአቅራቢያው የተመረተውን እህል እንዲከማች አደረገ።

49. ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ የሚሆን የእህል ሰብል አከማቸ፤ ሰብሉ እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ልኩን መስፈርና መመዝገብ አልቻለም ነበር።

50. ሰባቱ የራብ ዓመታት ከመምጣቱ በፊት፣ የሄልዮቱ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት ለዮሴፍ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደችለት።

51. ዮሴፍም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) መከራዬን ሁሉ፣ የአባቴንም ቤት እንድረሳ አድርጎኛል” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ምናሴ አለው።

52. እንደዚሁም፣ “መከራ በተቀበልኩበት ምድር እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፍሬያማ አደረገኝ” ሲል ሁለተኛ ልጁን ኤፍሬም አለው።

53. በግብፅ ምድር የነበረው ሰባቱ የጥጋብ ዘመን ዐለፈና

54. ዮሴፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረው የሰባቱ ዓመት የራብ ዘመን ጀመረ። ሌሎች አገሮች ሁሉ ሲራቡ፣ በመላው የግብፅ ምድር ግን ምግብ ነበር።

55. ራቡ በመላው የግብፅ ምድር መስፋፋት ሲጀምር፣ ሕዝቡ ምግብ ይሰጠን በማለት ወደ ፈርዖን ጮኸ። ፈርዖንም ግብፃውያኑን፣ “ወደ ዮሴፍ ሂዱና የሚላችሁን አድርጉ” አላቸው።

56. ራቡ በአገሩ ላይ እየተስፋፋ ስለሄደ፣ ዮሴፍ ጐተራዎቹን ከፍቶ እህሉ ለግብፃውያን እንዲሸጥ አደረገ፤ ምክንያቱም ራቡ በመላዪቱ ግብፅ ጸንቶ ነበር።

57. ራቡ በመላው ዓለም ጸንቶ ስለ ነበር፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ ከዮሴፍ ዘንድ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ምድር መጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 41