ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 41 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የፈርዖን ሕልም

1. ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለመ፤ በሕልሙም፣ በዐባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤

2. እነሆ መልቸው ያማረ፣ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር።

3. ቀጥሎም መልካቸው የከፋ ዐጥንታቸው የወጣ፣ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ።

4. እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፣ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጡአቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ።

5. ፈርዖንም እንደ ገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፣ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ።

6. ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ።

7. የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጡአቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር።

8. በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብፅ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፣ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጒምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም።

9. በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ።

10. በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር።

11. ሁለታችንም በአንዲት ሌሊት የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የየራሱ ትርጒም ነበረው።

12. በዚያን ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋር እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፣ ፍቺውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጐመልን፤

13. ነገሩም ልክ እርሱ እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ።

14. ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጒሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ።

15. ፈርዖንም ዮሴፍን፣ “ሕልም አይቼ ነበር፤ ሕልሜን ሊተረጒምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፤ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው።

16. ዮሴፍም ፈርዖንን፣ “እኔ የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለፈርዖን የሚሻውን ትርጒም ይሰጠዋል” አለው።

17. ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “በሕልሜ በአባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር።

18. ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው ያማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲበሉ አየሁ።

19. ከእነርሱም በኋላ፣ ዐቅመ ደካማ፣ መልካቸው እጅግ የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብፅ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም።

20. ዐጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን፣ ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጧቸው።

21. ከዋጧቸውም በኋላ፣ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደ ዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ።

22. እንደዚሁም፣ በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ፍሬያቸው የፋፋና ያማሩ ሰባት እሸት ዛላዎች ወጥተው አየሁ።

23. ቀጥሎም በምሥራቅ ነፋስ ተመተው የቀጨጩና የደረቁ ሌሎች ሰባት ዛላዎች ወጡ።

24. የቀጨጩት የእሸት ዛላዎችም ሰባቱን ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጧቸው፤ ይህንኑም ለአስማተኞች ነገርሁ፤ ነገር ግን ማንም ሊፈታው አልቻለም።”

25. ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዐይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ ፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል።

26. ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፣ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው።

27. ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው።

28. “አስቀድሜ ለፈርዖን እንደተናገርኩት፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል።

29. በመላው የግብፅ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ።

30. ከዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጐዳት፣ በግብፅ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም።

31. ከጥጋቡ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፣ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል።

32. ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ዘንድ የተቈረጠ ስለ ሆነ ነው፤ ይህንንም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል።

33. እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፣ በመላው የግብፅ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም።

34. እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፣ አንድ አምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኀላፊዎችን ይሹም።

35. እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ።

36. የሚከማቸው እህል፣ ወደ ፊት በግብፅ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።”

37. ዕቅዱንም ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት።

38. ፈርዖንም፣ “የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው።

39. ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፣ እንዳንተ ያለ አስተዋይና ብልኅ ሰው የለም።

40. አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።”

ዮሴፍ በግብፅ ተሾመ

41. ከዚያም፣ ፈርዖን ዮሴፍን “በመላዪቱ የግብፅ ምድር ላይ ኀላፊ አድርጌሃለሁ” አለው።

42. ፈርዖንም ባለማኅተሙን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ በዮሴፍ ጣት ላይ አደረገው፤ እንዲሁም ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በዐንገቱም የወርቅ ሐብል አጠለቀለት።

43. በማዕረግ ከእርሱ ሁለተኛ ሰው አድርጎ፣ በሠረገላ ላይ አስቀመጠው። ሰዎችም በፊቱ፣ “እጅ ንሡ” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾመው።

44. ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም በመላዪቱ ግብፅ ያላንተ ትእዛዝ እጁንም ሆነ እግሩን ልውስ የሚያደርግ አይኖርም” አለው።

45. ፈርዖንም ዮሴፍን ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ስም አወጣለት። እንዲሁም የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በመላዪቱ የግብፅ ምድር ተዘዋወረ።

46. ዮሴፍ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንን ማገልገል ሲጀምር፣ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ የግብፅን ምድር በሙሉ ዞረ።

47. በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ ሰብል ሰጠች።

48. በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመታት፣ ዮሴፍ በግብፅ አገር የተገኘውን ምርት ሰብስቦ በየከተሞቹ አከማቸ፤ በእያንዳንዱ ከተማ ከየአቅራቢያው የተመረተውን እህል እንዲከማች አደረገ።

49. ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ የሚሆን የእህል ሰብል አከማቸ፤ ሰብሉ እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ልኩን መስፈርና መመዝገብ አልቻለም ነበር።

50. ሰባቱ የራብ ዓመታት ከመምጣቱ በፊት፣ የሄልዮቱ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት ለዮሴፍ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደችለት።

51. ዮሴፍም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) መከራዬን ሁሉ፣ የአባቴንም ቤት እንድረሳ አድርጎኛል” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ምናሴ አለው።

52. እንደዚሁም፣ “መከራ በተቀበልኩበት ምድር እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፍሬያማ አደረገኝ” ሲል ሁለተኛ ልጁን ኤፍሬም አለው።

53. በግብፅ ምድር የነበረው ሰባቱ የጥጋብ ዘመን ዐለፈና

54. ዮሴፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረው የሰባቱ ዓመት የራብ ዘመን ጀመረ። ሌሎች አገሮች ሁሉ ሲራቡ፣ በመላው የግብፅ ምድር ግን ምግብ ነበር።

55. ራቡ በመላው የግብፅ ምድር መስፋፋት ሲጀምር፣ ሕዝቡ ምግብ ይሰጠን በማለት ወደ ፈርዖን ጮኸ። ፈርዖንም ግብፃውያኑን፣ “ወደ ዮሴፍ ሂዱና የሚላችሁን አድርጉ” አላቸው።

56. ራቡ በአገሩ ላይ እየተስፋፋ ስለሄደ፣ ዮሴፍ ጐተራዎቹን ከፍቶ እህሉ ለግብፃውያን እንዲሸጥ አደረገ፤ ምክንያቱም ራቡ በመላዪቱ ግብፅ ጸንቶ ነበር።

57. ራቡ በመላው ዓለም ጸንቶ ስለ ነበር፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ ከዮሴፍ ዘንድ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ምድር መጡ።