ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 47:12-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ዮሴፍም ለአባቱ፣ ለወንድሞቹና ለመላው የአባቱ ቤተ ሰዎች በልጆቻቸው ቍጥር ልክ ቀለብ እንዲሰፈርላቸው አደረገ።

13. በመላው ምድር እህል ባለመኖሩ ራቡ እየጸና ሄደ፤ ከዚህ የተነሣም ግብፅና ከነዓን በራብ እጅግ ተጐዱ፤

14. ዮሴፍ የግብፅና የከነዓን ሰዎች እህል በመሸመት የከፈሉትን ገንዘብ ሁሉ ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ቤተ መንግሥት አስገባ።

15. የግብፅና የከነዓን ሕዝቦችም ገንዘባቸው ባለቀ ጊዜ፣ ግብፃውያን ሁሉ ወደ ዮሴፍ ቀርበው፣ “የምንበላው እህል ስጠን፤ ገንዘባችን አልቆብናል፤ ዐይንህ እያየ እንዴት በራብ እንለቅ?” አሉት።

16. ዮሴፍም፣ “ከብቶቻችሁን አምጡ፤ ገንዘባችሁ ካለቀ በከብቶቻችሁ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ አለ።

17. ስለዚህ ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸው፣ በበጎቻቸው፣ በፍየሎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ለውጥ እህል ሰጣቸው። በከብቶቻቸው ልዋጭ ባገኙት ምግብ የዚያን ዓመት ራብ እንዲወጡት አደረገ።

18. ያም ዓመት ካለፈ በኋላ ሕዝቡ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዮሴፍ መጥተው እንዲህ አሉት፣ “እንግዲህ ከጌታችን የምንሰውረው ምንም ነገር የለም፤ ገንዘባችን አልቆአል፤ ከብቶቻችንንም አስረክበንሃል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው፣ ከመሬታችንና ከእኛ ከራሳችን በስተቀር፣ አንዳች ነገር የለም።

19. ታዲያ፣ እያየኸን እንዴት እንለቅ? መሬታችንስ ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንና መሬታችንን ውሰድና በለውጡ እህል ስጠን፤ እኛ የፈርዖን ገባሮች እንሁን፤ መሬታችንም የእርሱ ርስት ይሁን፤ እኛም እንዳንሞት መሬታችንም ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምን ዘራው ዘር ስጠን።”

20. ስለዚህ ዮሴፍ የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ራቡም እጅግ ስለጸናባቸው ግብፃውያን ሁሉ አንዳቸውም ሳይቀሩ መሬታቸውን ሸጡ፤ ምድሪቱም የፈርዖን ርስት ሆነች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 47