ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 3:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት መካከል የነበረው ጦርነት ብዙ ጊዜ ቈየ፤ ዳዊት እየበረታ ሲሄድ፣ የሳኦል ቤት ግን እየተዳከመ መጣ።

2. ዳዊት በኬብሮን ሳለ፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤የበኵር ልጁ፣ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን፣

3. ሁለተኛው፣ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ የተወለደው ኪልአብ፣ ሦስተኛው፣ ተልማይ ከተባለው ከጌሹር ንጉሥ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም፣

4. አራተኛው፣ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፤ አምስተኛው፣ ከአቢጣል የተወለደው ሰፋጥያ፣

5. ስድስተኛው፣ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትረኃም ነበር፤ እነዚህ ዳዊት በኬብሮን ሳለ የተወለዱለት ናቸው።

6. የሳኦል ቤትና የዳዊት ቤት በጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ፣ አበኔር በሳኦል ቤት ላይ ኀይሉን ያጠናክር ነበር።

7. ሳኦልም የኢዮሄልን ልጅ ሪጽፋን በቁባትነት አስቀምጦአት ነበር፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፣ “ለምንድን ነው ከአባቴ ቁባት ጋር የተኛኸው?” አለው።

8. አበኔርም በኢያቡስቴ ንግግር እጅግ ስለተቈጣ እንዲህ አለ፤ “እኔ ለይሁዳ የምወግን የውሻ ጭንቅላት ነኝን? ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹና ለዘመዶቹ ታማኝነቴን እስከ ዛሬ ድረስ አላጓደልሁም፤ አንተንም አሳልፌ ለዳዊት አልሰጠሁም፤ አሁን ግን አንተ ከዚህች ሴት ጋር በፈጸምሁት ነገር ትከሰኛለህን?

9. እግዚአብሔር ለዳዊት በመሐላ የሰጠውን ተስፋ እዳር እንዲደርስ ሳላደርግ ብቀር እግዚአብሔር በአበኔር ላይ ክፉ ያድርግበት፤ ከዚያ የባሰም ያምጣበት፤

10. የማለለትም መንግሥትን ከሳኦል ቤት አውጥቶ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባለው በእስራኤልና በይሁዳ ምድር ላይ የዳዊትን ዙፋን ለመመሥረት የሰጠው ተስፋ ነው።”

11. ኢያቡስቴም አበኔርን አጥብቆ ፈርቶት ስለ ነበር፣ እንደ ገና አንዲት ቃል እንኳ ሊመልስለት አልደፈረም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 3