ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 3:11-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ኢያቡስቴም አበኔርን አጥብቆ ፈርቶት ስለ ነበር፣ እንደ ገና አንዲት ቃል እንኳ ሊመልስለት አልደፈረም።

12. ከዚያም አበኔር ለዳዊት፣ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋር ተስማማ፤ እነሆ እስራኤል ሁሉ ወደ አንተ አንዲመለስ እኔ እረዳሃለሁ” ብለው ለዳዊት እንዲነግሩለት መልክተኞች ላከ።

13. ዳዊትም፣ “ይሁን እሺ፣ ከአንተ ጋር ስምምነቱን አደርጋለሁ፣ ነገር ግን ከአንተ አንዲት ነገር እሻለሁ፤ ይኸውም ወደ እኔ ስትመጣ በመጀመሪያ የሳኦልን ሴት ልጅ ሜልኮልን ይዘህልኝ እንድትመጣ ነው፤ ያለዚያ ግን ወደ እኔ እንዳትመጣ” አለ።

14. ከዚያም ዳዊት፣ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልክተኞች ላከበት።

15. ስለዚህም ኢያቡስቴ መልክተኛ ልኮ፣ ሜልኮልን ከባሏ ከሌሳ ልጅ ከፈልጢኤል ወሰዳት።

16. ባሏም እስከ ብራቂም ከተማ ድረስ እያለቀሰ ተከትሎአት ሄደ፤ ከዚያም አበኔር፣ “በል በቃል! ወደ ቤትህ ተመለስ” አለው። ስለዚህም ተመለሰ።

17. አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ተመካከረ፤ እንዲህም አለ፤ “ባለፈው ጊዜ ዳዊት በላያችሁ እንዲነግሥ ፈልጋችሁ ነበር፤

18. እግዚአብሔር ለዳዊት፣ ‘በባሪያዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ተስፋ ስለ ሰጠው፣ ይህን አሁኑኑ አድርጉት።”

19. እንዲሁም አበኔር ለብንያማውያን ራሱ ሄዶ ይህንኑ ነገራቸው፤ ከዚያም እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለጉትን ሁሉ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ።

20. አበኔር ከሃያ ሰዎች ጋር ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጣ፤ ዳዊትም ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 3