ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አሞጽ 9:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. በቀርሜሎስ ጫፍ ላይ ቢሸሸጉም፣አድኜ ፈልጌ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤እይዛቸዋለሁም፤በጥልቅ ባሕር ውስጥ ከእኔ ቢሸሸጉም፣በዚያ እባቡ እንዲነድፋቸው አዘዋለሁ፤

4. በጠላቶቻቸው ተነድተው ለምርኮ ቢወሰዱም፣በዚያ እንዲገድላቸው ሰይፍን አዛለሁ፤ለመልካም ሳይሆን ለክፉ፣ዓይኔን በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ።

5. ጌታ፣ እግዚአብሔር ጸባኦት፣ምድርን ይዳስሳል፤እርሷም ትቀልጣለች፤በውስጥዋ የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤የምድር ሁለመና እንደ ዐባይ ወንዝ ይነሣል፤እንደ ግብጽ ወንዝም ይወርዳል።

6. መኖሪያውን በሰማይ የሚሠራ፣መሠረቱንም በምድር የሚያደርግ፣የባሕርን ውሃ የሚጠራ፣በምድርም ገጽ ላይ የሚያፈስ፣እርሱ ስሙ እግዚአብሔር ነው።

7. “እናንት እስራኤላውያን፣ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን?”ይላል እግዚአብሔር“እስራኤልን ከግብጽ፣ፍልስጥኤማውያንን ከከፍቶር፣ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?

8. “እነሆ፤ የጌታ እግዚአብሔር ዐይኖች፣በኀጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፤ከምድር ገጽ፣ ፈጽሜ አጠፋዋለሁ፤የያዕቆብን ቤት ግን፣ ሙሉ በሙሉአልደመስስም፤”ይላል እግዚአብሔር።

9. “እነሆ፤ ትእዛዝ እሰጣለሁ፤እህል በወንፊት እንደሚነፋ፣የእስራኤልን ቤት፣በሕዝብ ሁሉ መካከል እንዲሁ አደርጋለሁ፤ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም።

10. በሕዝቤ መካከል ያሉ፣‘ክፉ ነገር አያገኘንም ወይም አይደርስብንም’ የሚሉ፣ኀጢአተኞች ሁሉ፣በሰይፍ ይሞታሉ።

11. “በዚያ ቀን፣የወደቀውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፤የተሰበረውን እጠግናለሁ፤የፈረሰውን ዐድሳለሁ፤ቀድሞ እንደነበረም አድርጌ እሠራዋለሁ፤

12. ስለዚህ የኤዶምን ትሩፍ፣በስሜ የተጠሩትንም ሕዝቦች ሁሉ ይወርሳሉ፤”ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አሞጽ 9