ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 7:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሙሴ የማደሪያ ድንኳኑን ተክሎ ካበቃ በኋላ ማደሪያ ድንኳኑንና ዕቃዎቹን ሁሉ ቀባቸው፤ ቀደሳቸውም፤ እንደዚሁም መሠዊያውንና ዕቃዎቹን በሙሉ ቀባቸው፤ ቀደሳቸውም።

2. ከዚያም የእስራኤል አለቆች ሆነው ከተቈጠሩት ነገዶች ኀላፊዎች የነበሩት የየቤተ ሰቡ መሪዎች ስጦታቸውን አቀረቡ።

3. ስድስት የተሸፈኑ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት በሬዎች ይኸውም ከያንዳንዱ አለቃ አንዳንድ በሬ እንዲሁም ከየሁለቱ አለቆች አንድ ሠረገላ ስጦታ አድርገው ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አመጡ፤ እነዚህንም በማደሪያው ድንኳን ፊት አቀረቧቸው።

4. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

5. “በመገናኛውም ድንኳን ለአገልግሎት እንዲውሉ እነዚህን ከእነርሱ ተቀበል፤ ለእያንዳንዳቸውም ለአገልግሎታቸው በሚያሰፈልጋቸው መጠን ለሌዋውያኑ ስጣቸው።”

6. ስለዚህ ሙሴ ሠረገሎቹንና በሬዎቹን ወስዶ ለሌዋውያኑ ሰጣቸው፤

7. ለጌድሶናውያን ለአገልግሎታቸው በሚያስፈልጋቸው መጠን ሁለት ሠረገሎችና አራት በሬዎች ሰጠ።

8. ለሜራሪያውያንም ለአገልግሎታቸው በሚያስፈልጋቸው መጠን አራት ሠረገሎችና ስምንት በሬዎች ሰጠ። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ኀላፊነት የሚመሩ ነበሩ።

9. በኀላፊነት የተሰጧቸውን ንዋያተ ቅዱሳት በትከሻቸው መሸከም ስለነበረባቸው፣ ሙሴ ለቀዓታውያን ምንም አልሰጣቸውም።

10. መሠዊያው በተቀባበት ቀን አለቆች የመሠዊያውን መቀደስ ምክንያት በማድረግ ስጦታዎችን አመጡ፤ በመሠዊያውም ፊት አቀረቡ።

11. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “የመሠዊያውን መቀደስ ምክንያት በማድረግ እያንዳንዱ አለቃ ስጦታውን በቀን በቀኑ ያቅርብ” አለው።

12. በመጀመሪያው ቀን ስጦታውን ያቀረበው ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበር፤

13. ስጦታውም፣ እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣

14. ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣

15. ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣

16. ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣

17. እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ አምስት አውራ በግ፣ አምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ። እንግዲህ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 7