ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 34:13-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም፣ በእኅታቸው በዲና ላይ ስለ ተፈጸመው ነውር፣ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው፣ ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር መልስ ሰጡ፤

14. እንዲህም አሉአቸው፤ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ብንሰጥ ውርደት ስለሚሆንብን፣ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም።

15. ሆኖም የምንስማማበት አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ ይህም ወንዶቻችሁን ሁሉ ገርዛችሁ እኛን የመሰላችሁ እንደሆነ ነው።

16. ከዚያ በኋላ ሴቶች ልጆቻችንን እንድርላችኋለን፤ አብረን እንኖራለን፤ አንድ ሕዝብም እንሆናለን።

17. በመገረዙ የማትስማሙ ከሆነ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።”

18. ያቀረቡትም ሐሳብ ለኤሞርና ለልጁ ለሴኬም መልካም መስሎ ታያቸው።

19. ከአባቱ ቤተ ሰብ ሁሉ እጅግ የተከበረው ይህ ወጣት የያዕቆብን ልጅ እጅግ ወዶአት ስለ ነበር፣ ያሉትን ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም።

20. ስለዚህ ኤሞርና ልጁ ሴኬም ይህንኑ ለወገኖቻቸው ለመንገር ወደ ከተማቸው በር ሄዱ፤

21. እንዲህም አሏቸው፤ “እነዚህ ሰዎች ወዳጆቻችን ናቸው፤ በአገራችን እንዲኖሩ፣ ተዘዋውረውም እንዲነግዱ እንፍቀድላቸው፤ ምድሪቱ እንደሆን ለእኛም ለእነርሱም ትበቃለች። ሴቶች ልጆቻቸውን እናገባለን፤ እነርሱም የእኛን ሴቶች ያገባሉ።

22. ሆኖም ሰዎቹ ከእኛ ጋር እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው አብረውን ለመኖር ፈቃደኞች የሚሆኑት፣ የእኛ ወንዶች እንደ እነርሱ የተገረዙ እንደሆነ ብቻ ነው።

23. ታዲያ እንዲህ ብናደርግ ከብታቸው ንብረታቸው፣ እንስሶቻቸው ሁሉ የእኛው ይሆኑ የለምን? ስለዚህ ባሉት እንስማማ፤ እነርሱም አብረውን ይኑሩ።”

24. ከከተማዪቱ በር ውጪ የተሰበሰቡት ሁሉ በኤሞርና በልጁ በሴኬም ሐሳብ ተስማሙ፤ በከተማዪቱም ያሉት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ።

25. በሦስተኛውም ቀን የሁሉም ቍስል ገና ትኵስ ሳለ ከያዕቆብ ልጆች ሁለቱ፣ የዲና ወንድሞች ስምዖንና ሌዊ፣ ሰይፋቸውን መዘው ሳይታሰብ ወደ ከተማዪቱ ገብተው ወንዶቹን በሙሉ ገደሏቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 34