ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 41:2-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እነሆ መልቸው ያማረ፣ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር።

3. ቀጥሎም መልካቸው የከፋ ዐጥንታቸው የወጣ፣ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ።

4. እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፣ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጡአቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ።

5. ፈርዖንም እንደ ገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፣ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ።

6. ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ።

7. የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጡአቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር።

8. በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብፅ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፣ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጒምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም።

9. በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ።

10. በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር።

11. ሁለታችንም በአንዲት ሌሊት የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የየራሱ ትርጒም ነበረው።

12. በዚያን ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋር እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፣ ፍቺውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጐመልን፤

13. ነገሩም ልክ እርሱ እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ።

14. ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጒሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ።

15. ፈርዖንም ዮሴፍን፣ “ሕልም አይቼ ነበር፤ ሕልሜን ሊተረጒምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፤ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው።

16. ዮሴፍም ፈርዖንን፣ “እኔ የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለፈርዖን የሚሻውን ትርጒም ይሰጠዋል” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 41