ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 49:16-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. “ዳን፣ ከእስራኤል ነገዶች እንደ አንዱ ሆኖ፣በራሱ ሕዝብ ላይ ይፈርዳል።

17. ዳን የመንገድ ዳር እባብ፣የመተላለፊያም መንገድ እፉኝት ነው፤ጋላቢው የኋሊት እንዲወድቅ፣የፈረሱን ሰኮና ይነክሳል።

18. “እግዚአብሔር ሆይ (ያህዌ)፤ ማዳንህን እጠባበቃለሁ።

19. “ጋድን ወራሪዎች አደጋ ይጥሉበታል፤እርሱ ግን ዱካቸውን ተከታትሎ ብድሩን ይመልሳል።

20. “አሴር ማእደ ሰፊ ይሆናል፤ለነገሥታትም የሚስማማ ምግብ ያቀርባል።

21. “ንፍታሌም ነጻ እንደ ተለቀቀች፣የሚያማምሩም ግልገሎችእንደምትወልድ ሚዳቋ ነው።

22. ዮሴፍ፤ ፍሬያማ የወይን ተክል፣በምንጭ ዳር የተተከለ ወይን ነው።ሐረጎቹ ቅጥርን ያለብሳሉ።

23. ቀስተኞች በጭካኔ አጠቁት፤በጥላቻም ነደፉት።

24. ነገር ግን በያዕቆብ ኀያል አምላክ ክንድ፣እረኛው በሆነው በእስራኤል ዐለት፣ ቀስቱ ጸና፤ጠንካራ ክንዱም ቀለጠፈ።

25. አንተን በሚረዳህ በአባትህ አምላክ፣በሚባርክህ፣ ሁሉን ማድረግ በሚችል አምላክ፣ከላይ ከሰማይ በሚገኝ ረድኤት፣ከምድር ጥልቅ በሚገኝ በረከት፣ከማሕፀንና ከጡት በሚገኝ ምርቃት ይባርክሃል።

26. ከጥንት ተራሮች በረከት፣ከዘላለም ኰረብቶች ምርቃት ይልቅ፣የአባትህ በረከት ይበልጣል፤ይኸ ሁሉ በዮሴፍ ራስ ላይ ይውረድ፤በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ግንባር ላይ ይረፍ።

27. ብንያም፣ ነጣቂ ተኵላ ነው፤ያደነውን ማለዳ ይበላል፤የማረከውን ማታ ይከፋፈላል።

28. እነዚህ ሁሉ ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው። ይህም እያንዳንዳቸውን ተገቢ በሆነው በረከት አባታቸው ሲባርካቸው የተናገረው ቃል ነው።

29. ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ወገኖቼ የምሰበሰብበት ጊዜ ደርሶአል፤ በኬጢያዊው በኤፍሮን ዕርሻ ውስጥ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ዘንድ ቅበሩኝ፤

30. ይህ በከነዓን ምድር፣ በመምሬ አጠገብ፣ በማክፌላ ዕርሻ ውስጥ ያለው ዋሻ፣ የመቃብር ቦታ እንዲሆን አብርሃም ከኬጢያዊው ኤፍሮን ላይ ከነዕርሻ ቦታው የገዛው ነው።

31. በዚያ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ተቀብረዋል፤ በዚያ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ተቀብረዋል፤

32. እኔም ልያን የቀበርኋት እዚያው ነው። ዕርሻውና ዋሻው የተገዙት ከኬጢያውያን ላይ ነው።”

33. ያዕቆብ እነዚህን ቃላት ለልጆቹ ተናግሮ እንዳበቃ፣ እግሮቹን በዐልጋው ላይ ሰብስቦ፣ የመጨረሻ ትንፋሹን ተነፈሰ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 49