ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የጋብቻ ምሳሌ

1. ወንድሞች ሆይ፤ ሕግን ለሚያውቁ ሰዎች እናገራለሁ፤ ሕግ በአንድ ሰው ላይ ሥልጣን የሚኖረው፣ ሰውየው በሕይወት እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑን አታውቁምን?

2. አንዲት ያገባች ሴት ከባሏ ጋር በሕግ የታሰረች የምትሆነው እርሱ በሕይወት እስካለ ድረስ ነው፤ ባሏ ቢሞት ግን ከጋብቻ ሕግ ነጻ ትሆናለች።

3. ነገር ግን ባሏ በሕይወት እያለ ሌላ ሰው ብታገባ አመንዝራ ትባላለች፤ ባሏ ቢሞት ግን ሌላ ሰው ብታገባም እንኳ፣ ከዚያ ሕግ ነጻ ትሆናለች፤ አመንዝራ አትባልም።

4. ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተም በክርስቶስ ኢየሱስ ሥጋ ለሕግ ሞታችኋል፤ ይህም ከሙታን ለተነሣው ለእርሱ፣ ለሌላው ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ ነው።

5. ኀጢአተኛ በሆነ ተፈጥሮ ቊጥጥር ሥር ሳለን፣ ለሞት ፍሬ እንድናፈራ በሕግ የተቀሰቀሰው የኀጢአት መሻት በሥጋችን ላይ ይሠራ ነበር።

6. አሁን ግን ቀድሞ ጠፍሮ አስሮን ለነበረው ሞተን፣ ከሕግ ነጻ ወጥተናል፤ ይህም አሮጌ በሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፣ አዲስ በሆነው በመንፈስ መንገድ እንድናገለግል ነው።

ከኀጢአት ጋር መታገል

7. እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ በራሱ ኀጢአት ነውን? በፍጹም አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ በኩል ባይሆን ኖሮ፣ ኀጢአት ምን እንደሆነ ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ “አትመኝ” ባይል ኖሮ፣ ምኞት ምን እንደሆነ በርግጥ አላውቅም ነበር።

8. ኀጢአት ግን ትእዛዙ ባስገኘው ዕድል ተጠቅሞ በእኔ ውስጥ ማንኛውንም ዐይነት አጒል ምኞት አስነሣ፤ ኀጢአት ያለ ሕግ ምዉት ነውና።

9. ሕጉ ሳይኖር ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ ከመጣ በኋላ ግን፣ ኀጢአት ሕያው ሆነ፤ እኔም ሞትሁ።

10. ለሕይወት እንዲሆን የታሰበው ያ ትእዛዝም ሞትን እንዳመጣ ተገነዘብሁ፤

11. ኀጢአት በትእዛዝ በኩል የተገኘውን ዕድል በመጠቀም አታለለኝ፤ በትእዛዝም ገደለኝ።

12. ስለዚህ ሕጉ በራሱ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፣ ጻድቅና መልካም ነው።

13. ታዲያ በጎ የሆነው ነገር ሞት ሆነብኝን? ከቶ አይደለም፤ ነገር ግን ኀጢአት በኀጢአትነቱ ይታወቅ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር በኩል ሞትን አመጣብኝ፤ ይኸውም ኀጢአት በትእዛዝ በኩል ይብሱን ኀጢአት ይሆን ዘንድ ነው።

14. ሕጉ መንፈሳዊ እንደሆነ እናውቃለን፤ እኔ ግን ለኀጢአት እንደ ባሪያ የተሸጥሁ ሥጋዊ ነኝ።

15. የማደርገውን አላውቅም፤ ለማድረግ የምፈልገውን አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ያን አደርጋለሁና።

16. ማድረግ የማልፈልገውን የማደርግ ከሆነ፣ ሕጉ በጎ እንደሆነ እመሰክራለሁ፤

17. እንዲህ ከሆነ፣ ይህን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው።

18. በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነው ተፈጥሮዬ ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐውቃለሁ፤ በጎ የሆነውን የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመው አልችልም።

19. የማደርገው ላደርገው የምፈልገውን በጎ ነገር አይደለም፤ ዳሩ ግን ለማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር ነው።

20. ላደርገው የማልፈልገውን ነገር የማደርገው ከሆነ፣ ያን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው።

21. ስለዚህ ይህ ሕግ እየሠራ እንደሆነ ተረድቻለሁ፤ ይኸውም በጎ ነገር ለመሥራት ስፈልግ፣ ክፋት ከእኔ ጋር አለ።

22. በውስጤ በእግዚአብሔር ሕግ ሐሤት አደርጋለሁ፤

23. ነገር ግን በብልቶቼ ውስጥ ለሚሠራው የኀጢአት ሕግ እኔን እስረኛ በማድረግ፣ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋ ሌላ ሕግ በብልቶቼ ውስጥ ሲሠራ አያለሁ።

24. እኔ ምን ዐይነት ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ሊያድነኝ ይችላል?

25. በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን።እንግዲያስ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ ባሪያ ስሆን፣ በኀጢአተኛ ተፈጥሮዬ ግን ለኀጢአት ሕግ ባሪያ ነኝ።