ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 7:5-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ኀጢአተኛ በሆነ ተፈጥሮ ቊጥጥር ሥር ሳለን፣ ለሞት ፍሬ እንድናፈራ በሕግ የተቀሰቀሰው የኀጢአት መሻት በሥጋችን ላይ ይሠራ ነበር።

6. አሁን ግን ቀድሞ ጠፍሮ አስሮን ለነበረው ሞተን፣ ከሕግ ነጻ ወጥተናል፤ ይህም አሮጌ በሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፣ አዲስ በሆነው በመንፈስ መንገድ እንድናገለግል ነው።

7. እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ በራሱ ኀጢአት ነውን? በፍጹም አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ በኩል ባይሆን ኖሮ፣ ኀጢአት ምን እንደሆነ ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ “አትመኝ” ባይል ኖሮ፣ ምኞት ምን እንደሆነ በርግጥ አላውቅም ነበር።

8. ኀጢአት ግን ትእዛዙ ባስገኘው ዕድል ተጠቅሞ በእኔ ውስጥ ማንኛውንም ዐይነት አጒል ምኞት አስነሣ፤ ኀጢአት ያለ ሕግ ምዉት ነውና።

9. ሕጉ ሳይኖር ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ ከመጣ በኋላ ግን፣ ኀጢአት ሕያው ሆነ፤ እኔም ሞትሁ።

10. ለሕይወት እንዲሆን የታሰበው ያ ትእዛዝም ሞትን እንዳመጣ ተገነዘብሁ፤

11. ኀጢአት በትእዛዝ በኩል የተገኘውን ዕድል በመጠቀም አታለለኝ፤ በትእዛዝም ገደለኝ።

12. ስለዚህ ሕጉ በራሱ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፣ ጻድቅና መልካም ነው።

13. ታዲያ በጎ የሆነው ነገር ሞት ሆነብኝን? ከቶ አይደለም፤ ነገር ግን ኀጢአት በኀጢአትነቱ ይታወቅ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር በኩል ሞትን አመጣብኝ፤ ይኸውም ኀጢአት በትእዛዝ በኩል ይብሱን ኀጢአት ይሆን ዘንድ ነው።

14. ሕጉ መንፈሳዊ እንደሆነ እናውቃለን፤ እኔ ግን ለኀጢአት እንደ ባሪያ የተሸጥሁ ሥጋዊ ነኝ።

15. የማደርገውን አላውቅም፤ ለማድረግ የምፈልገውን አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ያን አደርጋለሁና።

16. ማድረግ የማልፈልገውን የማደርግ ከሆነ፣ ሕጉ በጎ እንደሆነ እመሰክራለሁ፤

17. እንዲህ ከሆነ፣ ይህን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው።

18. በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነው ተፈጥሮዬ ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐውቃለሁ፤ በጎ የሆነውን የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመው አልችልም።

19. የማደርገው ላደርገው የምፈልገውን በጎ ነገር አይደለም፤ ዳሩ ግን ለማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር ነው።

20. ላደርገው የማልፈልገውን ነገር የማደርገው ከሆነ፣ ያን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 7